Fana: At a Speed of Life!

ጄኔራል አበባው ታደሰ ከደቡብ ሱዳን አቻቸው ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር መከላከያ ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ከደቡብ ሱዳን አቻቸው ሌተናል ጄኔራል ቶይ ቻኒይ ሬይት ጋር ተወያይተዋል፡፡
በምክትል ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ የተመራ የልዑካን ቡድን በጁባ የሥራ ጉብኝት በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ወቅትም ከደቡብ ሱዳኑ አቻቸው ሌተናል ጄኔራል ቶይ ቻኒይ ሬይት እና ቡድናቸው ጋር መወያየታቸውን ከደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚሁም ወቅት የኢትዮጵያው ወገን በሎጂስቲክስና በአቅም ግንባታ ጉዳዮች ለደቡብ ሱዳን ወገን ድጋፍ ለማድረግና ተሞክሮ ለማጋራት እንዲሁም የሁለቱ አገራት የድንበር አካባቢ ፀጥታና ደህንነትን ከማረጋገጥ አኳያ በትብብር ለመሥራት ከስምምነት ተደርሷል።

በሌላ በኩል በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ታባን ዴንግ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው የሁለቱ አገራት የመሠረተ-ልማት ግንኙነትን ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ተነጋግረዋል።
በዚሁም ወቅት ከኢትዮጵያ በኩል እስከ ድንበር አካባቢ ድረስ ያለው መንገዶች ግንባታ በጥሩ ደረጃ እንደተገነባ የተጠቀሰ ሲሆን ÷ ከደቡብ ሱዳን በኩል ግን የሚጠበቁ ሥራዎች እንዳሉ ተነስቷል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ደቡብ ሱዳንን በኢትዮጵያ በኩል ከጁቡቲ ወደብ ጋር የማገናኘት አካል የሆነውና በቅርቡ ሥራው የሚጀመረው ጋምቤላን ከደቡብ ሱዳን አፔር ናይል ጋር የሚያገናኝ መንገድ ግንባታ ላይ ለሚሣተፉ ኮንስትራክሽን ድርጅቶች በኢትዮጵያ በኩል ተገቢ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል፡፡
አምባሳደሩም ተገቢው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.