Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አገር አቀፉን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን በሀዋሳ አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አገር አቀፉን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን በሀዋሳ አስጀመሩ።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ከክልል እና ፌደራል መንግስታት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም ከአካባቢው ሀገር ሽማግሌዎችጋር በመሆን ነው በጋራ በታቦር ተራራ ላይ ዘመቻውን ያስጀመሩት።
 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክትም በኮቪድ-19 ምክንያት ዕድገታችን አይገደብም ብለዋል።
 
ዛሬ እየተከበረ ያለውን የዓለም የአካባቢ ቀን ምክንያት በማድረግ ነው ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ቀን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሯን በዛሬው እለት ያስጀመረችው።
 
ዘመቻው ኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወትን ለማስጠበቅ እና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ዕድገትን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጥረት ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
 
መርሃ ግብሩ በፌዴራል ደረጃ በሀዋሳ ቢጀመርም በሌሎች የአገሪቷ አካባቢዎች ችግኝ ተከላ እንደሚካሄድ መንግስት አስታውቋል።
 
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የወቅቱ ስጋት እንደመሆኑም የአረንጓዴ አሻራ ቀን የችግኝ ተከላ መርሃግብር ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከሚደረገው ጥንቃቄ ጋር ተጣጥሞ ይካሄዳል ብሏል።
 
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል እቅድ ተይዟል።
 
በስነ ስርዓቱ ላይ በዚህ ዝናባማ ወቅት በአንድ በኩል የኮቪድ-19ን በመከላከል በሌላ በኩል ደግሞ 5 ቢልዮን ችግኞችን ለመትከል በቤተሰብ እና በማኅበረሰብ ደረጃ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን የኮሮናቫይረስን በጥብቅ በመከላከል ሁሉም ኢትዮጵያዊ የ2012 ችግኝ ተከላን በንቃት እንዲሳተፍ ብሔራዊ ጥሪ ቀርቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.