Fana: At a Speed of Life!

ጣና ሀይቅ ሞልቶ ባስከተለው ጎርፍ መጥለቅለቅ በምስራቅ ደንቢያ ወረዳ ከ5 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተፈናቀሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጣና ሀይቅ ሞልቶ ባስከተለው የጎርፍ መጥለቅለቅ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ ከ5 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል።

በምስራቅ ደንቢያ ወረዳ አዲስጌ ድጌ፣ አቸራ፣ ሰራባ ፣ ዳብሎና ጣና ወይን ቀበሌዎች 935 አባዎራና እማውራ ጣና በመሙላቱ ተፈናቅለዋል።

የተፈናቃዮቹ አጠቃላይ ቁጥርም ከ5 ሺህ በላይ መሆኑን የወረዳው ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ አገኘሁ አስማረ ተናግረዋል።

ተፈናቃዮቹ በዘመድ ፣በትምህርት ቤቶች እና በማህበራት ተጠግተው የሚገኙ ሲሆን፥ በሀይቁ መጥለቅለቅ የውሃ ቧንቧዎች ጉዳት ስለደረሰባቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ ለማግኘት ተቸግረናል ብለዋል።

በተጨማሪም 5 ሺህ 962 ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ ማሽላ፣ በቆሎ፣ ሩዝ፣ ጤፍ እና በርበሬ ማሳ መውደሙን አቶ አገኘሁ ገልፀዋል።

ጣና ሀይቅ ሞልቶ ባስከተለው የጎርፍ መጥለቅለቅ እያደረሰ ያለው ጉዳት አሁንም እየቀጠለ ይገኛል ብለዋል ቡድን መሪው።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ፥ ለተፈናቃዮች እስካሁን 500 ሸራ፣ 16 የመጠለያ ድንኳን እና 1 ሺህ ካርቶን ብስኩት ድጋፋ መደረጉን ገልፀዋል።

1 ሺህ 113 ኩንታል እህል፣ ዘይት እና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ለማድረግ በሂደት ላይ መሆኑን የተናገሩት ሃላፊዋ፥ ከዞን እና ከክልል ጋር እየሰሩ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል።

በአገኘሁ አበባው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.