Fana: At a Speed of Life!

ጥራጥሬ እና የሱፍ ዘይት የጫኑ አራት መርከቦች ከዩክሬን ተንቀሳቀሱ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 1 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ የንግድ ሸቀጦችን የጫኑ አራት መርከቦች በዛሬው እለት ከዩክሬን መንቀሳቀሳቸው ተሰማ።

መርከቦቹ ከኦዴሳ እና ቾርኖሞርስክ ወደቦች የተነሱ ሲሆን፥ በቦስፎረስ የባሕር ወሽመጥ ጉዟቸውን ያደርጋሉ ተብሏል።

ከአራቱ መርከቦች ውስጥ ሁለቱ መዳረሻቸውን ቱርክ ሲያደርጉ ቀሪዎቹ ደግሞ ጣልያን እና ቻይና ሸቀጣቸውን ያራግፋሉ ተብሏል።

መርቦቹ የዩክሬንን የጥራጥሬ ምርቶች እና የሱፍ ዘይት ምርት የጫኑ መሆናቸውን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።

በዛሬው እለት ከተንቀሳቀሱት መርከቦች በተጨማሪም ለጭነት የተዘጋጀች ባዶ መርከብ ቾርኖሞርስክ ወደብ መድረሷንም ዘገባው አመላክቷል።

ባለፈው ሳምንት 27 ሺህ ቶን በቆሎ የጫነች መርከብ ከኦዴሳ መነሳቷ ይታወሳል።

ከሁለት ሳምንት በፊት በተመድ እና ቱርክ አደራዳሪነት የዩክሬንን እህል ለዓለም ገበያ ለማቅረብ በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ስምምነት መደረሱ ይታወሳል።

በስምምነቱ መሰረት ጥራጥሬ የጫኑ የዩክሬን መርከቦች ያለገደብ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፥ ሩሲያም መርከቦቹ እህል ጭነው በሚጓዙበት ወቅት የተኩስ አቁም የምታደርግ ይሆናል።

ቱርክም በተመድ ድጋፍ እየተደረገላት በአካባቢው የመሳሪያ ዝውውር እንዳይኖር በሚል ከሩሲያ በኩል የተነሳውን ስጋት ለመቅረፍ በመርከቦቹ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ታደርጋለች።

ለ120 ቀናት ተግባር ላይ የሚውለው ይህ ስምምነት በሁለቱ ወገኖች ከታመነበት እንደ ሁኔታው ሊራዘም ይችላል ነው የተባለው።

ስምምነቱን ተከትሎ ከዩክሬን ወደብ እየተንቀሳቀሰ ያለው የወጪ እህል ንግድ ለዓለም አቀፉ ገበያ እፎይታ ያመጣል ተብሎም ታምኖበታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.