የግላኮማ ህመም ምልክቶች ምንድን ናቸው?
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ግላኮማ የአይን ህመም በአይን ነርቭ ላይ ችግር የሚያስከትል ሲሆን በአይን ውስጥ የሚገኘው ግፊት በመጨመሩ ምክንያት የሚከሰት ነው።
የዚህ ግፊት መጨመር በአይናችን የምናያቸውን ምስሎች ወደ አንጎል የሚውስደውን የአይናችንን ነርቭ ይጎዳል፡፡
ይህም በቀጣይነት ቋሚ ለሆነ የአይን ብርሃን እጦት ይዳርጋል።
ግላኮማ በሚጀምርበት ጊዜ የሚያሳየው ቀዳሚ ምልክት ወይም የህመም ስሜት ስለሌለ ማንኛውም ሰው መደበኛ የሆነ የአይን ህክምና ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
ይህም አይናችን ለከፋ ጉዳት ከመጋለጡ በፊት ህክምና እንድናደርግለት ይረዳናል፤ከ 40 ዓመት ዕድሜ በላይ ያሉ ሰዎች በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ሐኪም በመሄድ ምርመራ ማድረግ አለባቸው።
በግላኮማ የሚጠቁ እነማን ናቸው?
በግላኮማ የሚጠቁት ከአርባ ዓመት ዕድሜ በላይ የሆኑ፣ በግላኮማ የተጠቃ ቤተሰብ ያላቸው፣ የስኳር ህመምተኞችና የአይን ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ናቸው፡፡
የግላኮማ ህመም ምልክቶች ምንድን ናቸው?
በአብዛኛው ግላኮማ በቅድሚያ የህመም ምልክት ላያሳይ ቢችልም ከጊዜ በኋላ ግን የመጀመሪያ ምልክት የሚሆነው በጥግ በኩል የሚጀምር የአይን ብርሃን ችግር ነው።
ከምልክቶቹ ውስጥ ድንገተኛ የሆነ የአይን ህመም፣ከፍተኛ የራስ ምታት፣የአይን ብዥታ፣ጥርት ያለ እይታ አለመኖር፣የአይን መቅላት፣የአይን ብርሃን ማጣት፣የአይን እይታ ጥበት ናቸው፡፡
እነዚህ ሁኔታዎች ሲያጋጥምዎ በአፋጣኝ ወደ አይን ሐኪም መሄድ ይጠበቅብዎታል።