Fana: At a Speed of Life!

በሀሰት ሰነድ የመንግስት ይዞታ ላይ ካርታ የሰጡና ይዞታውን የሸጡ እስከ 13 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም በተጭበረበረ መንገድ 638 ካሬ ሜትር የመንግስት ይዞታ ላይ የማረጋገጫ ካርታ የሰጡና ይዞታውን ወስደው በመሸጥ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ተብለው ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ ግለሰቦች በጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ተወስኗል።

የግራ ቀኝ የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን መርምሮ የቅጣት ውሳኔ የወሰነው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

በዛሬው ቀጠሮ በጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ የተወሰነባቸው ተከሳሾች ቀደም ሲል ሳምራዊት ኪዳኔ ሀጎስ የተባለ መጠሪያ ስሟን ወደ ሲፈን አበራ የቀየረችው 1ኛ ተከሳሽ እንዲሁም ለምለም ኪዳኔ ሀጎስ የነበረውን ስሟን ወደ ሀቄ ዶሮ ገመቹ በመቀየር የነዋሪነት መታወቂያ አውጥታለች የተባለችው 2ኛ ተከሳሽ ሀቄ ዶሮ ገመቹ ፣ 3ኛ ይርገዶ ሙሉጌታ፣ 4ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ አበራ ፣ በአሁን ወቅት በጡረታ የተገለለው የቀድሞ የቦሌ ክ/ከተማ የመሬት ልማት ይዞታ አስተዳደር ይዞታ አጣሪ ባለሙያ መለስ አብጤ፣ ቴክኒክ አጣሪ ባለሙያ ቢኒያም ወንደሰን እና በግል ስራ ይተዳደራሉ የተባሉት ኦሊያድ በቀለና አሳምነው ተስፋዬ ናቸው።

ከእነዚህ ተከሳሾች ጋር ክስ ቀርቦበት የነበረው 7ኛ ተከሳሽ ማለትም የቦሌ ክ/ከተማ የሰነድ አልባ ዝግጅት ኃላፊ የነበረው በሃይሉ አባተን በሚመለከት ዘግይቶ በመቅረቡ ምክንያት ጉዳዩ ተነጥሏል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ-ህግ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 1 ሀ እና ለ፣ አንቀጽ 33 እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9/1 ሀ፣ ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ እና የታክስ አስተዳደር አዋጁን ተላልፈዋል በማለት የተከሳሾቹን የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በዚህም ባቀረበው በአንደኛው ክስ ዝርዝሩ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሾቹ በጥቅም በመመሳጠር ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 12 ስር የሚገኙ ይዞታዎችን ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች በሀሰተኛ ሰነድ የአርሶ አደር ልጅ ነን በማለት ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ እና የአርሶ አደር ኮሚቴ ቃለ ጉባዔ ሀሰተኛ ሰነዶችን በክፍለ ከተማው ይሰሩ ለነበሩት ከ5ኛ እስከ 7ኛ ተራ ቁጥር ለተጠቀሱ ተከሳሾች በማቅረብ የይዞታ ካርታ እንዲዘጋጅላቸው ማድረግ እና በተጭበረበረ መንገድ የወሰዱትን 638 ካሬ ሜትር ይዞታን ደግሞ ሸጠው በመንግስት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ተብለው በደረጃው የተከሰሱ ግለሰቦች ናቸው።

በዚህ መልኩ በተጭበረበረ መንገድ በ1ኛ ተከሳሽ ስም 112 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ ካርታ ተሰርቶ የመንግስት ባዶ መሬት መሰጠቱ የተገለጸ ሲሆን ፥ በ2ኛ ተከሳሽ ስም 200 ካሬ ሜትር ፣ በ3ኛ ተከሳሽ 326 ካሬ ሜትር እንዲሁም በ4ኛ ተከሳሽ ስም 500 ካሬ ሜትር የመንግስት ቦታ ላይ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲወስዱ መደረጉ ተጠቅሷል።

በተጭበረበረ መንገድ ከተወሰዱ ይዞታዎች ውስጥ 1ኛ ተከሳሽ በራሷ ስም የወሰደችውን ይዞታ እንዲሁም በ2ኛ እና በ3ኛ ተከሳሾች ስም የተወሰዱ ይዞታዎችን ውክልና በመውሰድ በ8ኛ እና በ9ኛ ተከሳሾች አግባቢነትና አሻሻጭነት ለሁለት ግለሰቦች መሸጣቸውም ጠቅሶ ዐቃቤ-ህግ በክሱ ላይ አስፍሯል።

ፍርድ ቤቱ በሁለተኛው ክስ ማለትም ሀሰተኛ ሰነዶችን አዘጋጅተው አቅርበዋል ተብለው የተከሰሱ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ላይ የቀረበው ክስ በሃሰተኛ ሰነድ የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት መሆኑን በአንደኛው ክስ መገለጹን ጠቅሶ ፥ ሁለተኛው ክስ በአንደኛው ክስ እንዲጠቃለል ብይን ሰጥቷል፡፡

በ3ኛ ክስ ደግሞ በ8ኛ እና በ9ኛ ተከሳሾች ላይ ተከሳሾቹ የይዞታውን ህጋዊነት ደብቀው ገዢዎችን በማግባባት ይዞታው ተሽጦ ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር ጥቅም ያገኙ ሲሆን ፥ 1ኛ ተከሳሽ የገንዘቡን ምንጭ ለመደበቅ ጃፓን ስሪት ቲዮታ ሞዴል የቤት መኪና መግዛቷ ተጠቅሶ ፥ በወንጀል የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል።

በ4ኛው ክስ ደግሞ 1ኛ ተከሳሽ አንደኛውን ይዞታ በ7 ሚሊየን 700 ሺህ ብር፣ ሌላኛውን ይዞታ ደግሞ በ17 ሚሊየን ብር ለዐቃቤ-ህግ ለ15ኛ እና ለ16 ኛ ምስክሮች ለሆኑ ግለሰቦች ከሸጠች በኋላ የሰነዱን ትክክለኛ ባህሪ በመደበቅ እያንዳንዳቸውን ይዞታዎች በ1 ሚሊየን ብር ብቻ እንደሸጠች በማድረግ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 123 ንዑስ ቁጥር 1ለ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ የቴንብር ቀረጥ ክፍያን መሰወር ወንጀል ክስ ቀርቦባት ነበር።

ክሱ ከቀረበባቸው ተከሳሾች መካከል 2ኛ፣ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ችሎት ባለመቅረባቸው ጉዳያቸው በሌሉበት ነው የታየው።

ሌሎቹ 1ኛ፣ 5ኛ፣ 6ኛ፣ 8ኛ እና 9ኛ ተከሳሾች ግን ክሱ ከደረሳቸው በኋላ የተከሰሱበት ድንጋጌ ዋስትና የማያሰጥ መሆኑን ተከትሎ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ተደርጓል።

ከዚህም በኋላ ተከሳሾቹ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ-ህግ 18 የሰው ምስክሮችንና ገላጭና አስረጂ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ-ህግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሾቹ በተለያዩ ቀናት ባቀረቡት የተናጠልና የጣምራ መከላከያ ማስረጃዎች ግን የዐቃቤ-ህግ ማስረጃን በተገቢው ማስተባበል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ የተላለፈባቸው ሲሆን ፥ 2ኛ፣ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች በሌሉበት ጥፋተኛ ተብለዋል።

ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ-ህግ ተከሳሾች ላይ ያቀረበውን የቅጣት ማክበጃ አስተያየትና ችሎት የቀረቡ አምስቱ ተከሳሾች ያቀረቡትን የቅጣት ማቅለያ አስተያየት መርምሮ ዛሬ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።

በዚህም ቀደም ሲል ሳምራዊት ኪዳኔ ሀጎስ የተባለ መጠሪያ ስሟን ወደ ሲፈን አበራ ቀይራ የነዋሪነት መታወቂያ አውጥታለች የተባለችው 1ኛ ተከሳሽን ያቀረበችው የቅጣት ማቅለያ አስተያየት ተይዞላት በእርከን 30 መሰረት በ13 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ ተወስኗል።

2ኛ ተከሳሽ በ2 ዓመት ከ9 ወር ጽኑ አስራትና በ4 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ የተቀጣች ሲሆን ፥ 3ኛ ተከሳሽ ደግሞ በ4 ዓመት ጽኑ እስራትና በ71 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ፣ 5ኛ ተከሳሽ 4 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራትና በ4 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ፣ 6ኛ ተከሳሽ በ5 ዓመት ጽኑ እስራትና በ2 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ፣ 8ኛ እና 9ኛ ተከሳሾች ደግሞ እያንዳንዳቸው በ12 ዓመት ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኗል።

ፖሊስ ያልተያዙ ሦስት ተከሳሾችን አፈላልጎ የተጣለባቸውን ቅጣት እንዲፈጽሙ ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ታዟል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.