Fana: At a Speed of Life!

በ2013 በጀት ዓመት 320 ሚሊየን ኩንታል ሲሚንቶ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የሲሚንቶ እጥረትን ለመቅረፍ በሀገር ውስጥ ከሚመረተው በተጨማሪ 320 ሚሊየን ኩንታል ሲሚንቶ ከውጪ ሀገር ተገዝቶ እንደሚገባ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
 
በኢትዮጵያ ኮንስትክሽን ስራ መሰረታዊ ግብዓት በሆነው የሲሚንቶ ምርት ላይ ከታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መታየቱ የሚታወስ ነው፡፡
 
ይህንንም ችግር ለመፍታት ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በርካታ የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰዱን በመግለፅ ነገር ግን አሁንም ችግሩ ሙሉ በሙሉ ባለመፈታቱ ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱን በሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ ተናግረዋል፡፡
 
መመሪያው የተዘጋጀው የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱና በዘርፉ ከአምራችና አስመጭ እስከ ችርቻሮ ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩትን በማስተሳሰር፣ የአቅርቦትና ስርጭት ቁጥጥር እየተደረገበት ለህብረተሰቡ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ የዋጋ ንረት እንዳይከሰትና የተረጋጋ የሲሚንቶ ግብይት ስርዓት እንዲኖር ለማስቻል መሆኑ ተጠቁሟል።
 
ይህም ከነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሆነም አቶ ወንድሙ ገልጸዋል፡፡
 
በመመሪያው መሰረትም በሀገር ውስጥ ከሚመረተው በተጨማሪ መስፈርቱን በሚያሟሉ አስመጪዎች አማካኝነት 320 ሚሊየን ኩንታል ሲሚንቶ ወደ ሀገር ውስጥ ገበያ እንደሚገባ ተነግሯል፡፡
 
የሲሚንቶ አስመጭዎቹ የኮንስትራክሽን ቁሳቁሶች፣ ብረታ ብረት፣ ብረታ ብረት ያልሆነ እና እስክራፕል አስመጪነት ፈቃድ ማውጣት የሚገባቸው ሲሆን የሚያስመጡትም ሲሚንቶ PPC እና OPC 42 ነጥብ 5 መሆን አለበት ተብሏል፡፡
 
የሚመጣው ሲሚንቶ በ3ኛ ወገን የተረጋገጠ የብቃት ደረጃ ያለው መሆን አለበት ያሉት ዳይሬክተሩ አንድ አስመጪ ከ3 ሺህ ቶን ያላነሰ ሲሚንቶ ማስመጣት እንዳለበትም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
 
እንዲሁም አስመጪዎች የሚያስመጡት ሲሚንቶ ከተመረተበት ቀን ጀምሮ ከ3 ወራት ያልበለጠው መሆን እንዳለበት እና በ90 ቀናት ውስጥ ማስመጣት መጀመር እንዳለባቸውም ተጠቁሟል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.