Fana: At a Speed of Life!

እነ ቀሲስ በላይ መኮንን በተጠረጠሩበት በሀሰተኛ ሰነድ የዶላር ዝውውር ወንጀል ክስ መመስረቻ ተፈቀደ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እነ ቀሲስ በላይ መኮንን በተጠረጠሩበት በሀሰተኛ ሰነድ የዶላር ዝውውር ወንጀል ክስ መመስረቻ ለዐቃቤ ህግ ተፈቅዷል።

የክስ መመስረቻውን የፈቀደው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።

የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መርማሪ ፖሊስ በቀሲስ በላይ መኮንን ፣ያሬድ ፍስሃ እና ዳባ ገናና በተባሉ 3 ተጠርጣሪዎች ላይ ሲያከናውን የቆየውን የምርመራ ማጣሪያ ስራን ማጠናቁን ጠቅሶ የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ህግ ማስረከቡን አስታውቋል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በመዝገቡ ላይ ተሰይሞ የምርመራ መዝገቡ ዛሬ መረከቡን ጠቅሶ ፥ ተመልክቶ ለመወሰን እንዲያስችለው በወ/መስ/ህ/ቁጥር 109 /1 መሰረት የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

በተጨማሪም ዐቃቤ ህግ የተጠረጠሩበት ወንጀል ድርጊት ሀሰተኛ ሰነድ መገልገልና ንግድ ባንክን ማታለል መሆኑን ጠቅሶ ፥ በሙስና አዋጁ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 እና አንቀጽ 32 ስር ሊያስከስሳቸው እንደሚችል ገልጿል።

ተጠርጣሪዎቹ ከ6 ሚሊየን ዶላር በላይ ጥቅም ሊገኝበት እንደነበር ከ10 ዓመት በላይ በሚያስቀጣ ድንጋጌ ሊያስከስሳቸው እንደሚችል ተናግሮ የጠየቀው ዐቃቤ ህግ ፥ የ15 ቀን የክስ መመስረቻ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ፥ በፖሊስ ሲከናወን የቆየው ምርመራን የሚመራው ዐቃቤ ህግ መሆኑን ጠቅሰው እንደ አዲስ መዝገቡን ተመልክቼ ለመወሰን 15 ቀን ክስ መመስረቻ ይሰጠኝ ማለቱ ተገቢ አይደለም በማለት የዐቃቤ ህግ ክስ መመስረቻ ጊዜ ጥያቄውን በመቃወም ተከራክረዋል።

ጠበቆቻቸው ክስ ባልተመሰረተበት ሁኔታ ላይ ከ10 ዓመት በላይ ሊያስቀጣ ይችላል ተብሎ በግምት ሊገለጽ አይገባም በማለት ተከራክረዋል።

ሰነዱ የቀረበው ለውጭ ሀገር ድርጅት ሂሳብ በመሆኑ በፀረሙስና አዋጅ ሊታይ እንደማይችል በመግለጽ በሙስና ሊከሰሱ ይችላሉ ተብሎ በዐቃቤ ህግ መገለጹ አግባብ አይደለም በማለት ተከራክረዋል።

በተጨማሪም ጠበቆቹ በ2 ኛ እና 3ኛ ተጠርጣሪዎች ላይ ምንም ተሳትፎ ባልተገለጸበት ሁኔታ ላይ አብረው በእስር መቆየታቸው እና ክስ መመስረቻ ጥያቄ መቅረቡን ተቃውመዋል።

ጠበቆቹ “ሰነዱ የቀሲስ በላይ ስም ሆነ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ስም ባልጠቀሰበት ሁኔታ ላይ ቅንነት በጎደለው መልኩ ወንጀል ተብሎ መቅረቡ አግባብ አይደለም” በማለት ጠበቆቹ መከራከሪያ ነጥብ አንስተዋል።

ቀሲስ በላይ የልማት ሰብሳቢ፣ በምዕመናኖቻቸው ዘንድ የሚታመኑና በተፈለጉ ሰዓት የሚቀርቡ መሆናቸውን ጠበቆቻቸው ገልጸው ፥ የዋስ መብታቸው እንዲከበርም ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ከጠበቃ ለተነሳ መከራከሪያ ነጥብ መልስ የሰጠ ሲሆን ÷ በዚህም ጠበቆቹ ዐቃቤ ህግ ምርመራውን ሲመራ ቆይቶ እንደ አዲስ ክስ መመስረቻ መጠየቁ አግባብ አይደለም በማለት ባነሱት መከራከሪያ ነጥብ ላይ ዐቃቤ ህግ ምርመራ መራን ማለት ወንጀል እንመረምራለን ማለት አይደለም እኛ የህግ ድጋፍ ነው የምንሰጠው በማለት መልስ ሰጥቷል።

በተጨማሪም በጠበቆች በኩል ቅንነት የጎደለው ተግባር ነው ተብሎ በተገለጸው ክርክርን በሚመለከት ስነ ስርዓታዊ አለመሆኑን በመጥቀስ ዐቃቤ ህግም ሆነ ተቋሙ ማንንም ለመጉዳት እንደማይሰራና ህግን ተከትሎ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራ ብቻ እንደሚሰራ አብራርቷል።

የውጭ ሀገር ሂሳብና ሰነድ በኢትዮጲያ ፀረሙስና አዋጁ ሊታይ የማይችል መሆኑን ጠበቆች የጠቀሱበትን ነጥብ በሚመለከት መልስ የሰጠው ዐቃቤ ህግ የማታለል ተግባር ሊፈጸም የነበረው ህጋዊ ሰውነት ባለው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆኑን ጠቅሶ ፥ ክፍያው ተፈጽሞ ቢሆንና ጉዳት ቢደርስ ተጎጂው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆኑን ጠቅሶ፤ መታየት ያለበት በሙስና አዋጁ 881 /2007 ስር ነው በማለት በመከራከር መልስ ሰጥቷል።

ሰነዱን በሚመለከት ደግሞ ሰነዱ ንግድ ባንክ ቀርቦ የነበረ መሆኑን በመጥቀስ በህዝባዊ ድርጅት ወይም በመንግስታዊ ድርጅት ስር የሚታይ ሰነድ በመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 23/3 ስር ይካተታል በማለት ተከራክሯል።

ወንጀል በሌለበት ወንጀል ተብሎ ሊቀርብ አይገባም በማለት ለቀረበ የጠበቆች መከራከሪያን በሚመለከት ደግሞ ዐቃቤ ህግ በወንጀል ህጉ ሞራላዊ፣ ህጋዊና ግዙፋዊ ጉዳዮችን ያሟላ የወንጀል ድርጊት መሆኑን ገልጾ ፥ በሙስና አዋጁ እንደሚካተትና ከ10 ዓመት በላይ ሊያስቀጣ በሚችል ድንጋጌ ስር ሊያስከስስ እንደሚችል ጠቅሶ መልስ ሰጥቷል።

2ኛ እና 3ኛ ተጠርጣሪዎች ምንም ተሳትፎ የላቸውም በተባለው ጉዳይ ላይ ዐቃቤ ህግ ግብረዓበር ናቸው በማለት በአዋጁ ከአንቀፅ 32 እስከ አንቀጽ 37 ድረስ ባለ ድንጋጌ ስር በግብረአበርነት ክስ ሊቀርብባቸው እንደሚችል ገልጾ ማብራሪያ ሰጥቷል።

የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት ወንጀል በሙስና አዋጁ ስር የሚታይና ዋስትና የሚያስከለክል መሆኑን ጠቅሶ ፥ ተጠርጣሪዎቹ ክስ እስኪመሰረትባቸው ባሉበት ማረፊያ ቤት እንዲቆዩ በማለት ዐቃቤ ህግ የጠየቀውን የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል።

ቀሲስ በላይ መኮንን ከአንድ ሣምንት በፊት በአፍሪካ ህብረት ቅጥር ጊቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ በአካል ቀርበው ሀሰተኛ የክፍያ ሰነዶችን በመያዝ ለ3 ግለሰቦች እና ለአንድ የግል ድርጅት ሂሳብ 6 ሚሊየን 50 ሺህ ዶላር ለማዘዋወር ለባንኩ ጥያቄ በመቅረቡና የያዙት የክፍያ ሰነድ ሀሰተኛ መሆኑ መረጋገጡን ተከትሎ በአፍሪካ ህብረት ጥበቃ ተይዘው ለፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ተላልፈው መሰጠታቸውን ተከትሎ በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ በፖሊስ የምርመራ ማጣሪያ ሲከናወንባቸው እንደነበር ይታወሳል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.