Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችን ስራ የማስኬድ ተግባር ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አስረከበ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተከናወኑት የ’ገበታ ለሀገር’ ፕሮጀክቶችን ስራ የማስኬድ ተግባር ዛሬ ለኢትዮጵ አየር መንገድ ስካይላይት ሆቴል አስረክቧል፡፡

በገበታ ለሀገር የተገነቡ ሎጆችን ስራ የማስኬድ ተግባርን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በስካይ ላይት ሆቴል ተቋሙ በኩል እንዲወጣ የስምምነት ፊርማ ሥነሥርዓት ተካሂዷል።

ከአራቱ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ሶስቱ ማለትም ሃላላ ኬላ ሎጅ፣ ጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ እና ወንጪ ኢኮ ሎጅ በቅርቡ መመረቃቸው የሚታወሰ ሲሆን የጎርጎራ ፕሮጀክት ስራም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።

በጠቅላይ ሚኒስሩ ከፍተኛ ትኩረት እና አመራር የተከናወነው የ’ገበታ ለሀገር’ ስራ የብሔራዊው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱ ማዕዘን የሆነውን ቱሪዝምን የማሳደግ አላማ ያለው መሆኑ ተመላክቷል።

ፕሮጀክቶቹ በመጀመሪያው ፋይናንስ የማሰባሰብ ምዕራፍ የኅብረተሰቡን ድጋፍ በሰፊው ያሰባሰቡ፣ በግንባታቸው ምዕራፍ ግዙፍ የስራ ዕድል የፈጠሩ ብሎም ታላላቅ የመሰረተ ልማት ስራዎች እንዲከናወን በር የከፈቱ መሆናቸውም ተገልጿል።

በፈጠራ የተሞላ የፕሮጀክት ስራ፣ አስተዳደር እና ፈጣን አፈፃፀም ምን ሊመስል እንደሚችል ማሳያም መሆናቸውም ተጠቁሟል።

ቀጣይ የስራ ማስኬድ እና ማስተዳደር ተግባሩ ለብሔራዊ ሰንደቅ ተሸካሚው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊነት መሰጠቱም የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ከማስቻሉም ባለፈ ለዓለም አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻነት ትውውቅ ከፍ ያለ ዕድል እንደሚፈጥር ተመላክቷል።

በመርሐ ግብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሮጀክቶቹን ለአማራ፣ ለኦሮሚያ እና ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት ርክክብ ማድረጉን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.