Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለኢትዮጵያዊያን የኩራት ምንጭ የሆነ ታላቅ ተቋም ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለለመላው ኢትዮጵያዊያን የኩራት ምንጭ የሆነ ታላቅ ተቋም ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በከንቲባዋ የተመራ የአስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች በኢፌዴሪ አየር ኃይል ጉብኝት አድርገዋል።

በጉብኝቱ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ አየር ኃይል ከተጣለበት ሀገራዊ ተልዕኮ ባሻገር በግብርናው ልማት በኩል ቀድሞ አላግባብ ጥቅም አልባ ተደርጎ የነበረውን የተቋሙን መሬት ወደ ልማት በመቀየር ያስመዘገበው ታላቅ ስኬት በሀገር ደረጃም አርዓያነት ያለው አኩሪ ስራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሰላም ወጥቶ ለመግባትም ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ለተያዘው የልማት ጉዞ የሀገር መከላከያ ያፀናው ሰላም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለመላው ኢትዮጵያዊያን የኩራት ምንጭ የሆነ ታላቅ ተቋም ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለሀገር ባለው ክብርና ዝና አንቱታን ያተረፈ ትልቅ ተቋም መሆኑን አንስተዋል።

የግዛት አንድነታችን እንዲሁም ሉዓላዊነታችን በማስጠበቅ ለሀገራችን መድህን የሆነ አንጋፋው የአቪዬሽን ተቋም ነው ብለዋል።

ቢሾፍቱ በሚገኘው የአየር ኃይል መምሪያ ግቢ ውስጥ እየተከናወነ ያለው የግብርና ልማት አስተዳደሩ ለጀመረው የሌማት ትሩፋትም ጭምር በአርዓያነት የሚወስዱት መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህ ሁሉ የተቋሙ ስኬት አሻራቸውን ላኖሩ አመራሮችና አባላት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ እንደገለጹት በሀገራችን የተጀመረው ተቋማትን ውብ እና ፅዱ አድርጎ የመገንባቱ ተግባር በአየር ኃይል ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀው የክብርት ከንቲባዋና ካቢኔያቸው በተቋሙ ያደረጉት ጉብኝት ትልቅ ፋይዳ ያለው የሞራል ስንቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከተቋማዊ ሪፎርሙ ወዲህ የአዲስ አበባ አስተዳደር በርካታ እገዛዎችን ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወቁት ሌተናል ጄኔራል ይልማ ለተደረገላቸው ድጋፍ ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ በተለይም ለከንቲባ አዳነች አቤቤ ልዩ አድናቆት እና ክብር እንዳላቸውም ገልፀዋል።

በዕለቱ የግብርናውን ልማት እና ሌሎች ከለውጡ ወዲህ የተሰሩ መሰረተ ልማቶችን ከንቲባ አዳነች አቤቤና ካቢኔያቸው ተዘዋውረው መመልከታቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.