Fana: At a Speed of Life!

ፈረንሳይና የሳህል ቀጠና አባል ሀገራት ወታደራዊ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) ፈረንሳይ እና የሳህል ቀጠና አባል ሀገራት በአካባቢው የሚስተዋለውን የሽብር ድርጊት መከላከል የሚያስችል ወታደራዊ ስምምነት ፈጽመዋል።

የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን  እና የሳህል ቀጠና አባል ሀገራት መሪዎች በትናንትናው ዕለት  በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በፈረንሳይ መክረዋል።

በውይይት መድረኩ አምስቱ የሳህል ቀጠና አባል ሀገራት ማለትም የማሊ፣ ኒጀር፣ ቡርኮናፋሱ፣ ቻድ እና ሞሪታኒያ መሪዎች ተሳትፈዋል።

በውይይታቸውም  በሳህል ቀጠና እየተስፋፋ የመጣውን የሽብር እንቅስቃሴ በጋራ መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸው ነው የተገለጸው።

ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን  ከአል ቃይዳ እና አይ ኤስ የሽብር ቡድኖችጋር ግንኙነት ያላቸው ጽንፈኛ ቡድኖች በአካባቢው የሚፈጽሙትን ጥቃት ለመከላከል በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ፈረንሳይ በቀጠናው 4 ሺህ 500 የሚደርሱ ወታደሮች ማሰማራቷን ያስታወሱት ማክሮን፥የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማስከበር ፈረንሳይ ቁርጠኛ አቋም እንዳላት ተናግረዋል።

በዚህ መሰረትም ፈረንሳይ ተጨማሪ 220 የሚሆኑ ወታደሮችን በቀጠናው የምታሰማራ መሆኑን ነው  የገለጹት።

የቀጠናው አባል ሀገራት መሪዎች በበኩላቸው በአካባቢው የሚፈጸመውን የሽብር ድርጊት ለመቆጣጠር የተለያዩ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ቡድኖች ሃይላቸውን በማጠናከር የሚያደርሱት ጥቃት  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን  ነው የተናገሩት።

በቀጣይ በአካባቢው የሚፈጸመውን  የሽብር ድርጊት በዘላቂነት ለማስወገድም ሀገራቱ ሃላፊነት በተሞላበት መልኩ  በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ተመላክቷል።

በውይይት መድረኩ ፈረንሳይ እና የሳህል ቀጠና አባል ሀገራት መሪዎች በአካባቢው የሚስተዋለውን የሽብር ድርጊት ለማስወገድ ያላቸውን ወታደራዊ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል።

ምንጭ፦ አልጀዚራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.