Fana: At a Speed of Life!

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ከወገንተኝነት ነጻ የሚያድርጉ የአሰራር ማሻሻያዎች ያስፈልጋሉ ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ከወገንተኝነት ነጻ የሚያደርጉ የአሰራር ማሻሻያዎች እንደሚያስፈልጉ በስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ ዶክተር ሄኖክ ጌታቸው ገለጹ።
ማሻሻያዎቹም አሁናዊ የፖለቲካ ሁኔታን ያገናዘቡና የዓለም አገራት ድምጽ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እንዲሰማ የሚያደርግ መሆን አለበት ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ለ12ኛ ጊዜ ዛሬ ውይይት ያደርጋል።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፣ አየርላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ኖርዌይና ኢስቶኒያ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ላይ እንዲወያይ ጥያቄ ያቀረቡ አገራት ናቸው።
በስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ ዶክተር ሄኖክ ጌታቸው የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚያካሄደው ተደጋጋሚ ስብሰባ አንዳንድ የምእራባውያን አገራት ድርጅቱን የፖለቲካ ፍላጎታቸው መጠቀሚያ እንዳደረጉት እንደሚያሳይ ለኢዜአ ገልጸዋል።
የመጨረሻ ግቡም እነዚህ አገራት ኢትዮጵያን በማዳከም ካላት መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ የሚመነጩ የፖለቲካ ፍላጎቶቻቸውን ማሳካት መሆኑንም ተናግረዋል።
አገራቱ በኢትዮጵያ ላይ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለመጫን ተመድን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትን እንደ ፖለቲካ መሳሪያ እየተጠቀሙ መሆኑን አመልክተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.አ.አ በ1945 የተመሰረተው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊ አገራት ፍላጎትን መሰረት አድርጎ መሆኑን ነው ዶክተር ሄኖክ ያስረዱት።
ድርጅቱ ላለፉት ሰባት አስርተ ዓመታት የተወሰኑ ኃያላን አገራት የፖለቲካ ፍላጎት ማስጠበቂያ ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።
ከ190 በላይ አባል አገራትን ያቀፈው ድርጅት፤ እየተከተለ ያለው አሰራር በዓለም ላይ ያሉ አሁናዊ የፖለቲካ ለውጦችን የማይወክል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ በዓለም ላይ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ቢቋቋምም አሁን ላይ በተቃራኒ መንገድ እየሄደ እንደሚገኝ ነው ተመራማሪው ያስረዱት።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተለይም የጸጥታው ምክር ቤት ከዚህ ቀደም በአፍሪካና በሌሎች አገራት ያሳለፋቸው ውሳኔዎች አገራቱን አለመረጋጋት ውስጥ በመክተት ለችግር መዳረጉን አመልክተዋል።
አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት ምክር ቤቱን በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈጸም እየሰሩ እንደሆነም አብራርተዋል።
በመሆኑም ድርጅቱ ከወገንተኝነት የፀዳ እንዲሆን የሚያስችሉ የአሰራር ማሻሻያዎች ያስፈልጉታል ነው ያሉት፡፡
ማሻሻያዎቹም የዓለም አሁናዊ የፖለቲካ ሁኔታን ያገናዘቡና የዓለም አገራት ድምጽ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እንዲሰሙ የሚያደርጉ መሆን እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡
አፍሪካን ጨምሮ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ የሌላቸው አህጉራትን ያማከሉ መሆን እንደሚጠበቅባቸውም እንዲሁ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ኮፊ አናን ጨምሮ ብራዚል፣ ጃፓን፣ ሕንድና ጀርመን ተመድ አሁን ያለውን የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ ያማከለ ማሻሻያ እንዲያደርግ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበረም አስታውሰዋል።
እንቅስቃሴው አሁን ዳግም መቀስቀሱንና ጥያቄውን በተደራጀ መልኩ ማካሄድ የሚያስችል የተቀናጀ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ያስፈልጋታል በሚል የተጀመረው እንቅስቃሴ በአፍሪካ ሕብረትና በሌሎች ቀጠናዊ ተቋማት አጀንዳ ሆኖ መቅረብ እንዳለበትና የአፍሪካ አገራትም በጉዳዩ ላይ የጋራ አቋም ሊኖራቸው እንደሚገባ ነው ዶክተር ሄኖክ ያስረዱት።
አፍሪካውያንና ሌሎች የዓለም ሕብረተሰብ የተመድ አሰራር ማሻሻያና የዓለም ኢ-ፍትሐዊ አሰራር ለመቀየር የሚደረገው እንቅስቃሴን መቀላቀል እንዳለባቸው አክለዋል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.