Fana: At a Speed of Life!

የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ድንበር አቋርጠው ህብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ እየተሠራ መሆኑ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በአኮቦ ወረዳ ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ድንበር አቋርጠው ህብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሠራ መሆኑን የወረዳዉ አስተዳደር አስታወቀ።
የአኮቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኮንግ ጋትዮቴ እንደገለጹት÷ ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙሩሌ ጎሳ ታጣቂዎች በተለያዩ ጊዜያት ድንበር አቋርጠዉ በመግባት ጥቃት ሲፈፅሙ ቆይተዋል።
በዚህም ታጣቂ ቡድኑ በሰዉ ህይወት ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ባለፈ ህፃናትንና የቁም እንስሳትን ሲዘርፉ እንደነበር ጠቅሰዉ÷በአሁኑ ወቅት ከክልሉ የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀትና የስጋት ቀጠናዎችን በመለየት መሰል ጥቃት እንዳይፈፀም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በወረዳዉ የኔትወርክና የመንገድ መሠረተ ልማት ባለመሟላቱ የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን በፍጥነት ለመፍታት አስቸጋሪ መሆኑን ገልፀዉ÷ መንግስት እነዚህ መሠረተ ልማቶች ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በሙርሌ ታጣቂዎች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸውና ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብ እህል ድጋፍ መደረጉን የገለጹት አስተዳዳሪው÷ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ መንግስት እያደረገ ያለዉን ጥረት አድንቀዋል።
የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኤጄንሲ ዋና ስራ አስኬያጂ አቶ ጋትቤል ሙን በበኩላቸው÷ ቀደም ሲል በአካባቢው ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት የዘጠኝ ሰዎች ህይዎት ማለፉን ገልጸዋል፡፡
የክልሉ መንግስት በጥቃቱ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ከ2 ሺህ 500 በላይ ወገኖች በ2 ሚሊየን ብር 600 ኩንታል በቆሎ በመግዛት ድጋፍ ማድረጉንም ነው የተናገሩት፡፡
ተፈናቃዮችም በተደረገላቸው ድጋፋ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ወደ ቀያቸዉ እስከሚመለሱ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.