Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል በዜጎች ላይ የጭካኔ ድርጊት እየፈፀመ በሚገኘው አሸባሪው ሸኔ ላይ የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በዜጎች ላይ የጭካኔ ድርጊት እየፈፀመ በሚገኘው አሸባሪው ሸኔ ላይ የተቀናጀ ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፥ የክልሉ መንግስት የልማት ስራዎችን ከማፋጠን በተጓዳኝ በአሸባሪው ሸኔ ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል ብለዋል።
አሸባሪው ሸኔ በክልሉ በዜጎች ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ከፍተኛ ግፍና በደል ሲፈጽም መቆየቱን ገልጸው፤ይህንን ቡድን የማጥፋት የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ህዝባዊ አደረጃጀትንና የአጎራባች ዞኖችን ቅንጅታዊ አሰራር በማጎልበት የአሸባሪውን ሸኔ እኩይ ተግባር በማክሸፍ የቡድኑን አባላት የመደምሰስና በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
በተሳሳተ አስተሳሰብ የሽብር ቡድኑን የተቀላቀሉ ወጣቶችን በአባቶች ምክር ወደ ህብረተሰቡ እንዲመለሱ፤ ፈቃደኛ ባልሆኑት ላይ ደግሞ የተቀናጀ የጸጥታ ማስከበር ስራ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
በፌዴራልና የክልል ጸጥታ ሃይሎች ቅንጅት በተወሰደ እርምጃም ቡድኑ ሲንቀሳቅስባቸው ከነበሩ አካባቢዎች መበታተን መቻሉን ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም ከሰሞኑ ሽብርተኛው ቡድን የሚፈጽመውን አሰቃቂ ወንጀል የተመለከቱ ሃሰተኛ መረጃዎች እየተሰራጩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም የክልሉ መንግስት የሸኔን ሽብር ቡድን እንደሚደግፍ እና በአንድ ብሄር ላይ ብቻ ያነጣጠረ ጥቃት የተፈፀመ ተደርጎ የሚሰራጨው መረጃ ትክክል አለመሆኑን አስረድተዋል።
አሸባሪው ሸኔ ብሔር ሳይለይ በመንግስት አመራሮች፣በአገር ሽማግሌ፣ አባገዳዎችና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ላይ ግድያና ዘረፋ እየፈፀመ ያለ አሸባሪ ቡድን መሆኑንም ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የክልሉ መንግስት ከክልሉ ሰላም ማስከበር ስራዎች ባሻገር ከክልሎች ጋር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እና ልማትን የሚያጠናክሩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በባህል ትስስር፣በሰላምና ጸጥታ እና በትምህርት መስኮች በጋራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በክልሎች ያደረጉት ሰሞነኛ ጉብኝትም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።
በተለይም ከኦሮሚያ አጎራባች ክልሎች ድንበር አካባቢ ባለብዙ ቋንቋ ትምህርት የሚሰጥባቸው የትምህርት ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸው፤ የኢፈ ቦሩ ትምህርት ቤቶች ፕሮጀክቶችም የዚህ አካል እንደሆኑ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ቋንቋዎችን አበልጽጎ ለልማት ለማዋል በክልሉ ባጀት በሚተዳደረው የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ የሚዲያ ተቋም ከ17 በላይ ቋንቋዎች ተደራሽ እየሆነ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.