Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካና አውሮፓ ኅብረቶች የጋራ ጉባዔ ላይ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአፍሪካን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን አከናውነዋል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ እና አውሮፓ ኅብረት የጋራ ጉባዔ ላይ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአፍሪካን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስኬታማ ተግባራት አከናውነዋል።

የአውሮፓ ኅብረትና የአፍሪካ ኅብረት የጋራ ጉባዔ በቤልጂየም ብራስልስ እየተካሄደ ሲሆን÷ በጉባዔው የሁለቱን ኅብረቶች አባል አገራትን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ እየመከረ ነው፡፡

በጉባዔው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባዔው ላይ የአፍሪካን ብሎም የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የሚያጠናክሩ ሃሳቦችን ያነሱ ሲሆን÷ ከዚህ ጎን ለጎንም የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ÷ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባዔው ባደረጉት ንግግር በተለይ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የተጎዳውን የአፍሪካ ኢኮኖሚ መደገፍ እንደሚገባ አጽኖት መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡

ወረርሽኙ በአፍሪካ ካሳደረው ተጽእኖ አንጻር እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን አንስተው÷ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማንሳታቸውንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ አካታች እድገት እንዲመጣ የፋይናንስ ትብብር ስራዎች አፍሪካን ማዕከል ያደረጉ እንዲሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአውሮፓ ኅብረት በአፍሪካ መሰረተ ልማትን ለማጠናከር የሚከናወኑ ተግባራትን ለመደገፍ ቃል የገባውን የ150 ቢሊየን ዮሮ ድጋፍ አድንቀው ፥ ሌሎች የልማት ድጋፎችም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መጠየቃቸውንም ነው የገለጹት፡፡

ለአፍሪካ የሚደረጉ ድጋፎች አጀንዳ 2063 እና የዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካትን ማዕከል ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስተሩ አንስተዋል።

ከዚህ አኳያ የአውሮፓ ኅብረት በተለይ አፍሪካዊያንን ይበልጥ እርስ በርስ ለማስተሳሰር የሚደረጉ ጥረቶችን እንዲደግፍ ጠይቀዋል ነው ያሉት፡፡

በቤልጂየም፣ ሉክሰንበርግና በአውሮፓ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛና አምባሳደር ሂሩት ዘመነ በበኩላቸው÷ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉባኤው ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፍሬያማ የሁለትዮሽ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ ከቀድሞዋ የአውሮፓ ኅብረት ፕሬዚዳንት ከነበሩት የስሎቬኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም ከወቅቱ የኅብረቱ ፕሬዚዳንትና የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ጋር ያደረጉት ውይይት በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ኅብረት መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር ረገድ ፍሬያማ እንደነበር አንስተዋል፡፡

ከሌሎች አገራት መሪዎች ጋር በመገናኘትም በኢትዮጵያ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ማሳወቅ መቻላቸውንም ነው የገለጹት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጓቸው የሁለትዮሸ ውይይቶች መንግስት በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን የሄደባቸው ርቀቶችን ማስገንዘባቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የገጠሟትን ችግሮች ተቋቁማ ለውጥ እያስመዘገበች ያለች አገር መሆኗን መናገራቸውንም ነው ያነሱት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በመስኖ እና አረንጓዴ ልማት እንዲሁም በስራ ፈጠራ መስክ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን እንዳብራሩም አምባሳደር ሂሩት ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ ኅብረቶች የጋራ ድንጋጌ ላይ ኢትዮጵያ ያነሳቻቸው በርካታ ሃሳቦች መካተታቸውን ገልጸው ፥ በአጠቃላይ በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካን ብሎም የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን ስለማከናወናቸው ማውሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.