Fana: At a Speed of Life!

በርዕሠ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የተመራ ልዑክ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በመስኖ የለማ የስንዴ ማሳ ጎበኘ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በርዕሠ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የተመራ ልዑክ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ደንዲ ወረዳ ጃዊ ቡሪ ቀበሌ በመስኖ የለማ የስንዴ ማሳ ጎበኘ፡፡

አርሶ አደሮች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በመስኖ ስንዴ በማምረት ላይ መሆናቸዉን ተናግረዋል።

የገንዘብ ሚንስቴር ሚኒስትር ዴኤታዉ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ እንደገለጹት÷ አርሶ አደሮቹ መስኖን በመጠቀምና በክላስተር በመደራጀት ስንዴን ለማምረት እያደረጉት ያለዉ ጥረት የሚበረታታ ነው።

ያለንን የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር የዉሃ በአግባቡ በመጠቀም በዓመት ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ ማምረት ከቻልን ሀገሪቱ የምትፈልገዉን የስንዴ ምርት በብዛት ማግኘት እንችላለን ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታዉ÷ በመስኖ መልማት ከሚችለዉ መሬት እስካሁን ድረስ የለማዉ በቂ ባለመሆኑ በደንዲ ወረዳ የታየዉን አይነት ልምድ ማስፋፋት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

በመንግስት በኩልም የመስኖን ልማት ለማዘመን ተገቢዉ ድጋፍ እየተደረገ ነዉ ብለዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ÷ በዞኑ በርካታ አርሶ አደሮች በክላስተር በመደራጀት በመስኖ ስንዴ በማምረት ላይ መሆናቸዉን ገልጸው÷ ለመስኖ ልማት የሚያገለግል መካከለኛና አነስተኛ ጀነሬተር በመንግስት በኩል ተደራሽ እየተደረገ ነው ማለታቸውን ኦቢኤን ዘግቧል፡፡

የዞኑ የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተረፈ አራርሳ እንደገለጹት÷ በዞኑ 27 ሺህ 596 ሄክታር መሬት ላይ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.