Fana: At a Speed of Life!

የሙሩሌ ታጣቂዎች በንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ ለሚያደርሱት ተደጋጋሚ ጥቃት መፍትሄ እንዲሰጠው ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሙሩሌ ታጣቂዎች የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው በንጹሃን ዜጎች ላይ ለሚያደርሱት ተደጋጋሚ ጥቃት መፍትሄ እንዲሰጠው አምባሳደር ነቢል ማህዲ ጠየቁ።
 
በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜዪኪ አዪ ዴንግ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
 
በውይይታቸውም አምባሳደር ነቢል በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የጋራ ድንበር ጋር የተያያዙ የጸጥታና የልማት ጉዳዮች ዙሪያ ለሚኒስትሩ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
 
በተለይም የሙሩሌ ታጣቂዎች የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው በንጹሃን ዜጎች ላይ ለሚያደርሱት ተደጋጋሚ ጥቃት መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
 
ለዚህም ይረዳ ዘንድ በቅርቡ የጋራ ድንበር ኮሚሽን ስብሰባ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ነው አምባሳደሩ የጠቆሙት።
 
ከዚህ ባለፈም መንገድን ጨምሮ ሁለቱን አገራት በተለያዩ መሠረተ ልማቶች በማስተሳሰር ተዋሳኝ ሕዝቦችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።
 
በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ መሻሻሉን ገልጸው፥ ለዚህም መንግሥት አገራዊ ምክክር ለማድረግ ሁኔታዎች ማመቻቸትን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ ጥረት እያደረገ መሆኑን አብራርተውላቸዋል።
 
ሜዪኪ አዪ በበኩላቸው÷ በጋራ ድንበሮች አካባቢ አስተማማኝ ሰላም ማረጋጋጥ እንዲሁም ሁለቱን አገራት የሚያዋስኑ ተጎራባች ማኀበረሰቦች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ የበለጠ ተቀራርቦ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
 
ከዚህ አንጻር የተጎራባች ክልሎች አመራሮች የጋራ ምክክር ለማድረግ የደቡብ ሱዳን ወገን ዝግጁ አንደሆነ ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.