Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ከኮሞሮስ አቻው ጋር ነገ የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ከኮሞሮስ አቻው ጋር ነገ የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግ ተገለጸ።

የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ 10 ሺህ 725 ተመልካቾች በሚያስተናግደው “ስታድ ኦምኒስፖርትስ ደ ማሉንዚ” ይካሄዳል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለጨዋታው ዝግጅት ይረዳው ዘንድ ለ30 ተጫዋቾች ጥሪ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፣ ጥሪ ካደረገላቸው ስድሥቱን በመቀነስ 23 ተጨዋቾችን ይዞ ወደ ኮሞሮስ ማቅናቱን ኢዜአ አመልክቷል።

ዳንኤል ተሾመ፣ዓለምብርሃን ይግዛው፣አብዱልከሪም ወርቁ፣በረከት ወልዴ፣ዊሊያም ሰለሞንና ፍጹም ጥላሁን ከቡድኑ የተቀነሱ ተጫዋቾች መሆናቸውም ነው የተጠቆመው፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ ከመጋቢት 9 ቀን ጀምሮ ዓ.ም ለጨዋታው ልምምድ ሲያደርግ የቆ ሲሆን በዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ ከተካተቱት ተጫዋቾች መካከል ለግብጹ ኤል ጉና ክለብ የሚጫወተው ሽመልስ በቀለ ይገኝበታል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የነገ ጨዋታ በካሜሮን አስተናጋጅነት ከተካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ በኋላ የመጀመሪያው ሲሆን፣ በውድድሩ ከነበረበት ምድብ አንድ ነጥብ ብቻ ይዞ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ሳይችል ቀርቷል።

የኮሞሮስ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ የሆኑት ፈረንሳዊው የኑስ ዜርዱክ ÷ ከዋልያዎቹ ጋር ላለባቸው ጨዋታ 24 ተጫዋቾች ጥሪ ያደረጉ ቢሆንም ሁሉም ተጫዋቾች ተሰብስበው ልምምድ መሥራት የጀመሩት ከጥቂት ቀናት በፊት ነው።

ከሁለት ሣምንት በፊት የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ሆነው የተሾሙት ትውልደ ሞሮኮዋዊው አሠልጣኝ የመጀመሪያ የሆነ ጨዋታቸውን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ያደርጋሉ።

‘ዘ ኮኤላካንትስ’ ወይም “አሳዎቹ” በሚል ቅጽል ስም የሚጠሩት የኮሞሮስ ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት የካሜሮኑ 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 16 ውስጥ መግባቷ የሚታወስ ነው።

ሁለት ግብ ጠባቂዎቿን ጨምሮ 12 ተጫዋቾቿ በኮቪድ-19 በመያዛቸው ምክንያት ከካሜሮን ጋር 16 ውስጥ ባደረገችው ጨዋታ የግራ መስመር ተመላላሹ ቻከር አልዱሃር በግብ ጠባቂነት አሰልፋ መጫዋቷ ይታወሳል።

በጨዋታው የቡድኑ አምበል ናጂም አብዱ በሰባተኛው ደቂቃ በቀይ የወጣባት ኮሞሮስ 2 ለ 1 ብትሸነፍም ተጫዋቾቹ በፈተና ውስጥ ያደረጉት ትግል በወቅቱ በብዙዎች ዘንድ አድናቆት ተችሮታል።

የኢትዮጵያና ኮሞሮስ ብሔራዊ ቡድኖች የነገው ጨዋታ የመጀመሪያ ግንኙነታቸው ነው።

የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ የኮሞሮስ ዳኞች በዋናና ረዳት ዳኝነት ይመሩታል።

በፊፋ የወንዶች ወርሃዊ የአገራት ደረጃ ኢትዮጵያ 138ኛ፤ ኮሞሮስ 131ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

 

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.