Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተመቻቸውን ሁኔታ ተጠቅሞ ለትግራይ የሚያደርገውን ድጋፍ ሊያሳድግ ይገባል – መንግሥት

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በመንግስት የቀረበውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ለትግራይ ሕዝብ የሚያደርገውን የእርዳታ መጠን ሊጨምር እንደሚገባ የኢትዮጵያ መንግሥት ገለፀ፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ በሰጠው መግለጫ÷ ባለፉት ሁለት ቀናት 50 ምግብና ነዳጅ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ከሠመራ ወደ ትግራይ ክልል መላካቸውን አስታውቋል፡፡
መግለጫው መንግሥት በትግራይ ክልል እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ በተገቢው መንገድ እንዲደርስ ለማስቻል የግጭት ማቆም ውሳኔ ማሳለፉን አስታውሷል፡፡
ይህንን ተከትሎም የሰብአዊ እርዳታን ወደ ክልሉ ለማድረስ በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ነው የገለፀው።
ከእነዚህም መካከል በየቀኑ የሚደረግ የአየር ትራንስፖርትን በማመቻቸት የእርዳታ አቅራቢ ተቋማት አቅም የፈቀደውን ያህል የመድሃኒት፣ የህክምና ቁሳቁስና አልሚ ምግብ እንዲያጓጉዙ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
በየብስ ትራንስፖርትም በመጀመሪያው ዙር የምግብ ድጋፍን የያዙ 21 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ መግባታቸው ተገልጿል፡፡
ባለፉት ሁለት ቀናት ደግሞ 47 የምግብ ድጋፍ የያዙና 3 ነዳጅ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች በድምሩ 50 የጭነት መኪኖች ከሠመራ ተነስተው ወደ መቀሌ ጉዞ እያደረጉ መሆኑን መግለጫው አመላክቷ፡፡
ተጨማሪ 10 የምግብ እርዳታን የያዙ የጭነት ተሽከርካሪዎችም ከሠመራ ጉዞ ጀምረዋልም ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደርሳቸው ለማድረግ የገባውን ቃል በማክበር ምቹ የሰብአዊ እርዳታ ማጓጓዣ ሁኔታን ለመፍጠር እየሠራ እንደሚገኝ ነው አገልግሎቱ ያስታወቀው፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ይህንን መንግሥት ያቀረበውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወደ ትግራይ የሚደርሰውን የእርዳታ መጠን ከፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል በአስቸጋሪ ሁኔታ ወስጥ የሚገኙት የክልሉ ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደርሳቸው ወራሪው ኃይል አሁንም ከያዛቸው የአፋርና አማራ ክልል አካባቢዎች እንዲወጣና ምቹ የእርዳታ ማስተላለፊያ መስመርን መዘርጋት እንዲቻል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያደርግም መንግሥት ጥሪውን አቅርቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.