Fana: At a Speed of Life!

በቂ እረፍት እንዴት ማግኘት ይቻላል?

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዶክተር ሳውንድራ ዳልተን ስሚዝ በጻፉት ‘’ሴክሬድ ሬስት’’ መፅሐፋቸው ላይ የሰው ልጅ ከድካም ተላቆ እንዴት በቂ እረፍት ሊያገኝ እንደሚችል ይጠቁማሉ።

ዶክተር ሳውንድራ እንደሚሉት የተለያዩ የእረፍት ዓይነቶች አሉ፤ እነዚህ የእረፍት ዓይነቶች በሰው ልጅ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ውጤታቸው ጎልቶ ይታያል፡፡

እንደ ዮጋ፣ ሰውነትን መሳሳብ እና ማሳጅ (መታሸት) ሰውነት ቀልጣፋ እና ጤናማ እንዲሆን ያግዛል ይላሉ።

መሰል እንቅስቃሴዎች ሰውነት ከድካም እና ከተለያዩ ጫናዎች እንዲያገግም እንደሚረዳም ይገልጻሉ።

ለሰው ልጅ ከሚያስፈልጉት አንደኛው የአዕምሮ እረፍት ነው የሚሉት ዶክተር ሳውንድራ፥ የአዕምሮ እረፍት ማግኘት የትኩረት ማጣት የእቅልፍ እጦትን ለማስተካከል እንደሚረዳም ያስረዳሉ።

የአዕምሮ እረፍት ራስን ማድመጥ መቻል መሆኑን በመጥቀስም ይህ የእረፍት ዓይነት እጅግ ጠቃሚ እንደሆነም ገልጸዋል።

ምክንያቱም አዕምሮ በተጨናነቀበት እና እረፍት ባጣበት ጊዜ ምንም አይነት ተግባር ለመፈጸም እንደሚቸገርም አስረድተዋል።

የስሜት እረፍት ሌላኛው የሰው ልጅ ሊያገኘነው የሚገባ የእረፍት ዓይነት ሲሆን ፥ ከተለያዩ የስራ ጫናዎችና ወከባ ገለል በማለት ለራስ እረፍት መስጠት ይቻላል።

ለአብነትም ኮምፒውተር ላይ ለብዙ ሰዓት በመቀመጥ ስራዎችን እያከናወኑ ከሆነ ጊዜ ወስዶ ከኮምፒውተር ብርሃኑ እና ከድምጾች ራስን በማራቅ እረፍት ወስዶ መመለስ ስራውንም ውጤታማ እንደሚያደርገውም ነው የሚገልጹት።

ራስን በፈጠራ ነገሮች ማሳረፍም ሌላው የእረፍት አይነት ነው።

ይህም ሲባል ተፈጥሮን ማድነቅ፣ ድራማ ወይም ፊልም መመልከት፣ ሙዚቃ ማዳመጥና መሰል ተግባራትን በመከወን ከተለመዱ እና ከተጨናነቁ ነገሮች አዕምሮ እና ሰውነትን በማራቅ ማዝናናት መቻል ነው፡፡

ከልብ ጓደኛ ፣ ቤተሰብ እና ሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን ራስን ማዝናናት እና ከተለምዷዊ ተግባር ገለል በማለት ልምዶችን በመለዋወጥና በመጫዎት ለራስ እረፍት መስጠት ይቻላል፡፡

የመንፈስ እረፍትም ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊው የእረፍት አይነት ነው።

የመንፈስ እረፍት ሁሉም የሰው ልጆች ከራሳቸው አልፈው ከሌሎች ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት ነው።

ይህን ደግሞ ሃይማኖታዊ ተግባር መፈጸም፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር የመንፈስ ግንኙነትን ማጠናከር እና መሰል ተግባራት መንፈሳዊ እረፍት ለመጎናጸፍ ያስችላሉ፡፡

እነዚህ የእረፍት ዓይነቶች በእያንዳንዱ ቀናቶች ጅምር ላይ የሚፈጥሩት ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

የቀናቶች ጅምር ደግሞ ሙሉ ውሎን የመቆጣጠር ሃይል ያላቸው ስለሆኑ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በህይወት እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳርፈው በጎ እና አሉታዊ ተጽዕኖ አለ፡፡

ከዚህ አንጻርም የሰው ልጆች በዚህ መልኩ ለራሳቸው በቂ እረፍት በመስጠት ራስን ከድካም ማራቅና ጤናማ ህይወትን መምራት ይችላሉ።

መረጃው የወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም ነው

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.