Fana: At a Speed of Life!

በድሬዳዋ 10 ሺህ ዜጎች የተሳተፉትበት የጎዳና ላይ የአብሮነት ኢፍጣር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳ ከተማ የረመዳን ጾምን ምክንያት በማድረግ 10 ሺህ የሚሆኑ የእስልምና እምነት ተከታዮች የተሳተፉበት የጎዳ ላይ ኢፍጣር ተካሂዷል።
 
በለገሀር አደባባይ በተካሄደው መርሐ ግብር ከፍተኛ የአስተዳደሩ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና በ10 ሺህዎች የሚገመቱ የእስልምና እምነት ተከታዮች ተሳትፈዋል፡፡
 
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ÷የፍቅርና የአብሮነት ተምሳሌት በሆነችው ድሬዳዋ የተዘጋጀው የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሐ ግብር የወንድማማችነት እና የአብሮነት እሴቶቻችን ይበልጥ በማጉላት አንድነታችንን ከማጠናከር አንጻር ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡
 
በፕሮግራሙ ላይ የተሳተፉ አካላትና መላው የአስተዳደሩ ነዋሪ ያሳየውን አንድነት በማጠናከር ለከተማዋ እድገት ከመንግስት ጎን በመሆን በማህበራዊና ኢኮኖማዊ ዘርፍ ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
በእስልምና ጉዳዮች የኡለማዎች ምክር ቤት አባል የሆኑት ሼኽ አሚን ኢብሮን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች ለህዝበ ሙስልሙ አንድነትና ከሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ጋር ማቻቻል እንደሚገባ እና በወንድማማችነት መንፈስ ለጋራ አገራዊ ሠላምና እድገት ላይ ያተኮሩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡
 
የዝክሪና የኢባዳ ወር በሆነዉ የረመዳን ወር ስንፆም ሚስኪኖችን በማሰብና በመርዳት መሆን አለበትም ማለታቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
የረመዳን ወርን በመተጋገዝና በመረዳዳት እያሳለፉ እንደሚገኙ የገለፁት ምእመናን በበኩላቸው፥ ቀሪውን የፆም ጊዜ ይህንኑ የመተሳሰብ እሴት ሃይማኖቱ በሚፈቅደው ሁሉ አጠናክረው ለመቀጠል ቃል ገብተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.