አሸባሪው ሸኔን የማፅዳቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኦሮሚያ ክልል ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪውን ሸኔ ከተለያዩ አካባቢዎች የማፅዳቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ፡፡
የክልሉ መንግስት ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፥ ሸኔ ባለፉት አራት ዓመታት በኦሮሞ ህዝብ ላይ የፈጸመው አስነዋሪ እና ጭካኔ የተመሞላበት ተግባር ቡድኑ ምንም አይነት የፖለቲካ አላማ እና ግብ እንደሌለው ማሳያ መሆኑን አንስቷል፡፡
ሰሞኑን በሽብር ቡድኑ ላይ የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደበት መሆኑን የጠቆመው መግለጫው፥ ይህን ተከትሎም ጊዜ ያለፈባቸው የቡድኑ አመራሮች በሰው ልጅ ላይ የማይደረግ ድርጊት በኦሮሞ ህዝብ ላይ ሲፈጽሙ መቆየታቸውን በራሳቸው ላይ መመስከር መጀመራቸውን አመላክቷል፡፡
የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ወጣት የሽብር ቡድኑ አባላትም ሰላማዊ መንገድን መርጠው በብዛት እጃቸውን እየሰጡ እንደሚገኙም ነው የጠቆመው።
የኦሮሞ ህዝብ ጥቅም በጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን በሃሳብ ልዕልና የሚከበር መሆኑን በመጠቆም ፥ መንግስት ቡድኑ በሰላማዊ መንገድ እንዲታገል ሰፊ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
ሸኔ ከመንግስትም ባለፈ ከመላው ኦሮሞ ህዝብ የሰላም ጥሪ ሲቀርብለት የቆየ ቢሆንም፥ቡድኑ የተቀበለውን የባንዳነት ተልዕኮ ለማሳካት እና የኦሮሞን ፖለቲካ ለመቀልበስ ቀን ከሌት የጠላትነት ተግባር መፈጸሙን ቀጥሎበታል ነው ያለው መግለጫው፡፡
በዚህ ምክንያት የኦሮሞ ህዝብ ባለፉት አራት አመታት በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የጭካኔ ተግባር ሲያስተናግድ ቆይቷል ፤ በዚህም ሸኔ ከኦሮሞ ህዝብ ባህል እና እሴት ጋር የሚጻረሩ አስነዋሪ እና ዘግናኝ ድርጊቶችን መፈጸሙ ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም የሽብር ቡድኑ ለዓመታት የተለፋባቸውን የተለያዩ የልማት ስራዎች በእሳት ከማጋየት ባለፈ የሚችለውን ሲዘርፍ እና በርካታ ዜጎችም በቡድኑ ጥቃት ትምህርትን የመሰሉ መሰረታዊ ፍላጎቶች እንዳይሟሉላቸው ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱን አመላክቷል፡፡
በሸኔ ሽብር ቡድን በክልሉ የሚፈጸሙ አስነዋሪ ድርጊቶችን በዘላቂነት ለማስወገድ ከሰሞኑ የተጀመሩ እርምጃዎች ውጤት እያስገኙ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው፥ በቀጣይም እርምጃው ተጠናከሮ እንደሚቀጥል አስገንዝቧል፡፡
እርምጃውን ተከትሎ የሽብር ቡድኑ አከርካሪ እየተሰባበረ ከመሆኑ ባሻገር አባላቱ በሰላም እጃቸው ለመንግስት እየሰጡ እና በራሳቸው ጊዜ እየተበታተኑ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
ሸኔ የኦሮሞ ህዝብ የምንጊዜም ጠላት መሆኑን በመጠቆም፥ የክልሉ መንግስት የሽብር ቡድኑን በመደምሰስ ለህዝቡ እፎይታ ለመስጠት አበክሮ እንደሚሰራ ነው ያስተወቀው፡፡
በሽብር ቡድኑ ላይ ተጀመረው የተቀናጀ እርምጃ በፍጥነት ውጤት እንዲያስመዘግብም ህብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋብ በመናበብ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ክልሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በመላኩ ገድፍ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!