Fana: At a Speed of Life!

የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ ክልሎች ለ1 ሺህ 443ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ ክልሎች ለ1 ሺህ 443ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1 ሺህ 443ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በተመሳሳይ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት÷ ይህ ወቅት እንደ ሀገር ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ በሆኑ ተከታታይ ቀውሶች እየተደራረቡ የተመላለሱበት ወቅት እንደመሆኑ የመሻገሪያ መንገዳችንም በእኩልነት የተመሰረተ አንድነት ላይ በምንገነባው ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት መሆኑን ከታሪካዊ ተሞክሯችንም ሆነ ከነባራዊ ሁኔታዎቻችን መረዳት ይገባናል ብሏል፡፡

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት÷ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል ፈጥር በዓልን ሲያከብር ፍቅርን፣ መተሳሰብንና አንድነትን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመው÷ በጾም ወራት ያሳየውን መተሳሰብ በበዓሉ ወቅትም ሆነ በሌሎቹም ጊዜያት መድገም እንዳለበትም ገልጸዋል::

በተመሳሳይ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ÷ በተለይ በዚህ የችግር ወቅት መላው ሕዝበ ሙስሊም በዓሉን በመደጋገፍ እና በመረዳዳት ሊያሳልፈው እንደሚገባ ጠቁመው÷ ለዚህም ከእምነቱ ድንቅ እሴቶች አንዱ የሆነውንና አቅሙ ያለው ሙስሊም በነፍስ ወክፍ የሚያወጣውን “የዘካተል ፍጥር” የእህል ስጦታ በማስተባበር በብዙ መልኩ ችግር ውስጥ ላሉ ሰዎች በማበርከት የወገን አለኝታነቱን እንዲወጣ እጠይቃለሁ ብለዋል፡፡

በሀገራችን እየተስተዋለ ያለው ጽንፈኝነት ከእምነቶች አስተምህሮት ባፈነገጠ መልኩ የግል ፍላጎት እና የፖለቲካ ትርፍ ማካበት በሚፈልጉ አካላት የሚፈጸም እንደሆነ ጠቁመው÷ ሕዝበ ሙስሊሙም ሆነ የሌላው እምነት ተከታይ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የጽንፈኝነት እንቅስቃሴዎችን የከፋ አደጋና ጉዳት እንዳያደርስ ካላከሸፈ የመጀመሪያ ተጎጂው ራሱ በመሆኑ ከወዲሁ አምርሮ በተደራጀ መልኩ መታገል ይኖርበታል ብለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት÷ የሀገራችን ሕዝብ ለዘመናት የተገመደበት የአብሮነት ገመድ በዚህ በዓል ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

በዓሉን ስናከብርም የአብሮነትና የሰላም እሴቶቻንን ከሚያጎድፉ ተግባራት በመታቀብ የኢትዮጵያን ከፍታ እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ሚና በመወጣት መሆን እንዳለበትም ነው ያመለከቱት፡፡

በተመሳሳይ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ባስተላለፉት የእንኳ አደረሳችሁ መልዕክት÷ “በረመዳን ፆም ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከምግብና ከመጠጥ ብቻ ሳይሆን እራሱን የሚያርቀው ከመጥፎ ሀሳብና ድርጊትም ጭምር ነው” መሆኑን ጠቁመው÷ ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን 1 ሺህ 443ኛውን ለኢድ አልፈጥር በዓል አደረሳችሁ ሲሉ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው÷ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

የኢድ አልፈጥር የመረዳዳት፣ የመተሳሰብና የአብሮነት በዓል ነው፤በቀጣዩም ጊዜ ይህንኑ መረዳዳትና አብሮነት በማጠናከር ሰላማችንን ዘላቂ የምናደርግበት ሊሆን ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤም ለመላ የእስልምና እምነት ተከታዮች ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳች መልዕክት÷ያሳለፋችሁት የአንድ ወር የሮመዳን የጾም ወቅት የመረዳዳት፣ የመተሳሰብ እና የአብሮነት ነበር፤ቀጣዩም ጊዜ ይህንኑ መረዳዳት እና አብሮነት በማጠናከር ሰላማችንን ዘላቂ የምናደርግበት፣ ይሁንልን ብለዋል።

የአፋር ክልለ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት÷ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብ፣ በመጠየቅ ማሳለፋችን በየዕለቱ ስናፈጥር ደስታችን ወደር አልነበረውም፤ በኢድ ወሳኝ ቀንም አቅም በፈቀደ መጠን ችግራቸውን ለመቅረፍ ጥረት ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

በረመዳን የታየው ወደ መልካም ነገር መሽቀዳደም፣ በሌላ ወራት የሚቋረጥ ሳይሆን ረመዳንን እንደ ትምህርት ቤት በመቁጠር ለቀጣይ ስንቅ የምንሰንቅበትና ከመጥፎ ተግባራት በመራቅ መልካም መስራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

በተመሳሳይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጆሀር ለኢድ- አልፈጥር በዓል ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ÷እስልምናን ጨምሮ ሁሉም ሃይማኖቶች መሰረታቸው ሰላም በመሆኑ በሃይማኖቶቹ ውስጥ ያሉ መልካም እሴቶችን በመጠቀም ለሰላም ሁሉም ዘብ መቆም ይገባል ብለዋል፡፡

ስለሆነም እምነቶችን መሰረት አድርገው ሊከፋፍሉን የሚፈልጉ ሃይሎችን በመታገል ሰላምና ወንድማማችነትን እንዲሁም መቻቻልን የበለጠ ለማጠናከር ተጋግዘን መስራት ይኖርብናልም ነው ያሉት፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድም 1 ሺህ 443ኛው ዓመተ ሂጅራ የዒድ አል-ፈጥር በዓልን አስመልክተው ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር ላይ ያደረገውን የእርስ በርስ መረዳዳት እና መደጋገፍ በመደበኛ ወቅትም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.