Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድቡን ጨምሮ በፋይናንስ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶች መክሸፋቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በህዳሴው ግድብ እና በከፍተኛ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶች ማክሸፉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ።
የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው የኢትዮጵያን ሰላምና ዕድገት በማይፈልጉ ሀገራት የሚደገፍ ድርጅት÷ የህዳሴው ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል በማቀድ ‘ብላክ ፒራሚድ ወር’ በሚል ስያሜ የሳይበር ጦርነት መክፈቱን ጠቁመው÷ ሙከራውም ጉዳት ሳያደርስ መክሸፉን አብራርተዋል፡፡
በተለይም የፋይናንስ ተቋማት የሚጠቀሙባቸውና እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ 37 ሺህ ኮምፒውተሮች ላይ ጥቃት በመፈጸም የህዳሴው ግድብን ለማስተጓጎል ተሞክሯል ብለዋል።
የህዳሴው ግድብ ኃይል ማመንጨት ከጀመረ በኋላ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶች ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ይገመታል ያሉት ዶክተር ሹመቴ÷ ለዚህም ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ተግባራዊ በማድረግ ከህዳሴው ግድብ ግንባታና ቁጥጥር ተቋማት ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ግድቡን በተመለከተ ከአመራረት እስከ ግንባታ ዕቃዎች ማጓጓዣ የሚያጠቃልሉ ሥራዎች ላይ የሳይበር ምህዳሩን በመጠቀም ከፍተኛ ክትትል ይደረጋል ብለዋል።
በተመሳሳይም በኢትዮጵያ ከፍተኛ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ በርካታ የሳይበር ጥቃቶች እንዲከሽፉ ተደርጓል ሲሉ ተናግረዋል።
ለዚህም የፋይናንስ ተቋማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚደረጉ የሳይበር ጥቃቶች ዒላማ መሆናቸውን ጠቁመው÷ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል ሁልጊዜም አንድ እርምጃ ቀድሞ ማየት፣ ማቀድና መተግበር ያስፈልጋል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡
አክለውም የተቃጡት ጥቃቶች ቢሳኩ ኖሮ በፋይናንስ ተቋማት ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ችግር ያስከትሉ እንደነበር ገልጸዋል።
በ2014 ዓ.ም ግማሽ ዓመት ከ3 ሺህ 400 በላይ ከፍተኛ እና አደገኛ የሆኑ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች እንደተመከቱ የገለጹት ዶክተር ሹመቴ÷ ተቋማቱም ከነዚህ ዓይነት ጥቃቶች ራሳቸውን ለመጠበቅና ለመከላከል አስፈላጊ የሚባሉ ዝግጅት ሊያደርፈጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.