አራት ኢትዮጵያውያን ዳኞች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታን እንዲመሩ ተመረጡ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አራት ኢትዮጵያውያን ዳኞች ማፑቶ ላይ የሚካሄደውን የሞዛምቢክ እና የሩዋንዳ ጨዋታ እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡
የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን÷ ከአንድ ወር በፊት የሀገራት ድልድል መከናወኑ ይታወሳል፡፡
በምድብ 12 ሴኔጋል፣ ቤኒን፣ ሞዛምቢክ እና ሩዋንዳ የተደለደሉ ሲሆን የምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ ከአንድ ወር በኋላ ይካሄዳል፡፡
በዚህ ምድብ ግንቦት 26 ማፑቶ ላይ የሚካሄደውን የሞዛምቢክ እና ሩዋንዳ ጨዋታ አራት ኢትዮጵያውያን ዳኞች እንደሚመሩት መመረጣቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡
በዚህም መሰረት÷ ኢንተርናሽናል አርቢትሩ ባምላክ ተሰማ በዋና ዳኝነት፣ ተመስገን ሳሙኤል እና ፋሲካ የኋላሸት በረዳት ዳኝነት እንዲሁም ቴዎድሮስ ምትኩ በአራተኛ ዳኛነት ጨዋታውን የሚመሩት ይሆናል፡፡