Fana: At a Speed of Life!

ከዓለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ ጉባኤ ጎን ለጎን የተደረጉ ውይይቶች የኢትዮጵያን እውነታ ያስረዱና ጥቅሟን ያስጠበቁ ናቸው – አቶ አህመድ ሺዴ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 27 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) የጸደይ ወቅት ጉባኤ ጎን ለጎን የተደረጉ ውይይቶች የኢትዮጵያን እውነታ ያስረዱና ጥቅሟን ያስጠበቁ መሆናቸውን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ተናገሩ።

በአሜሪካ በተካሄዱ ውይይቶች ዓለም ባንክ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ በዓለም አቀፉ የልማት ማህበር አማካኝነት ለኢትዮጵያ የ6 ቢሊየን ዶላር አዲስ ፕሮጀክት ለማጽደቅ ማቀዱንም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ በልማት ማዕቀፍ ውስጥ የባንኩ ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆኗ እንደሚቀጥልም ተነግሯል።

ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ጋር በተደረገው ቆይታም በቡድን 20 ሀገራት በጋራ ማዕቀፍ ውሳኔ መሰረት የዕዳ ሽግሽግ እንዲደረግ ቢወሰንም እስካሁን ሳይተገበር የቆየው ምክረ ሃሳብ ዳግም እንዲታይ ከስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል።

አይ ኤም ኤፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙን እንደሚደግፍና የውጭ ምንዛሪ ድጋፉን ለማስቀጠል የሚያስችሉ ውይይቶች እንዲካሄዱ ከስምምነት መደረሱን የገንዘብ ሚኒስትሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ከጉባኤው ጎን ለጎን ለአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያን እውነታ የሚያስረዳ የዲፕሎማሲ ስራ መሰራቱን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል የተፈጠረውን ብዥታ ከማጥራትና ግንኙነትን ከማደስ አንጻር ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

በዓለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ በኩል የሚታሰቡ ፕሮጀክቶች እንዲጸድቁ አሜሪካ ድጋፏን እንደምትሰጥ አረጋግጣለችም ነው ያሉት።

ግንኙነታቸው ወደ ቀደመ መልኩ እንደሚመለስና እንደመልካም ማሳያም ዓለም ባንክ በግጭት ምክንያት የተጎዱ አካበቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም 300 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ሲያጸድቅ አሜሪካ እና አጋሮቿ በሙሉ ድምጽ ድጋፉን ማጽደቃቸውን አውስተዋል።

በሰሜኑ ግጭት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የከፋ አቋም ይዞ የቆየው የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩ ኤስ ኤይድም ቢሆን ከዳይሬክተሯ ሳማንታ ፓወር ጋር የተደረገውን ውይይት ተከትሎ ያቋረጣቸውን ፕሮጀክቶች እንደሚያስቀጥልና ለመልካም ወዳጅነትም በድርቅ እና በግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች የሚውል ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑንም አስረድተዋል።

በአጠቃላይ በአሜሪካ የነበረው ቆይታ እጅግ ውጤታማ እና የኢትዮጵያን ጥቅም ያስከበረ ስለመሆኑም ነው የገለጹት።

አያይዘውም ድጋፎቹም ሆኑ የታደሰው ግንኙነት ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታን ታሳቢ ያላደረገ መሆኑን ጠቁመው፥ ውሳኔዎቹ ብዥታን ማጥራትና የኢትዮጵያን እውነታ ማሳወቅ በመቻሉ ከመረዳት የመነጨ ነው ብለዋል።

በባሃሩ ይድነቃቸው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.