ትሪፖሊ በታጠቂ ኃይሎች በተኩስ ታመሰች
አዲስ አበባ፣ግንቦት 9፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በሊቢያ በስልጣን ሽኩቻ ምክንያት በተፈጠረ ውዝግብ የታጠቁ ኃይሎች በትሪፖሊ ተኩስ መከፈታቸውን የሀገሪቱ ፓርላማ አስታወቀ፡፡
የሊቢያ ጦር አዛዥ ፊልድ ማርሻል ካሊፋ ሀፍጣር በሰጡት መግለጫ፥ በሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፖሊ የተከሰተው ግጭት የቀድሞው የሊቢያ አስተዳደር ለአዲሱ የፓርላማ ተወካይ ፋቲ በሻጋ ስልጣኑን ለማሰረከብ ፈቃደኛ ባለመሆኑ በተነሳ ውዝግብ ምክንያት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የቀድሞ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረሩትና ባለፈው የካቲት ወር የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ፋቲ በሻጋ ትሪፖሊ ከመግባታቸው ነው ከተማዋ ተኩስ በተኩስ የሆነችው።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፋቲ በሻጋ ከፊልድ ማርሻል ከሊፋ ሀፍጣር ጋር ያለችው ቅርበትም በተቃዋሚዎች ዘንድ አልተወደደላቸውም።
በሊቢያ ተቀናቃኝ አስተዳደሮች ለሁለት ወራት ከዘለቀው አለመግባባት በኋላ ፋቲ በሻጋ ትሪፖሊ መግባታቸው የተነገረ ሲሆን ከተማዋ ከገቡ ከሰዓታት በኋላ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ፊልድ ማርሻል ሀፍጣር ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ነከተማዋ ለሚኖሩ ዜጎች ሰላምና ደህንነት ሲሉ ከተማዋን ለቀው እንደወጡ ነው የገለጹት።
ዛሬ ጠዋት ላይ የከባድ መሳሪያዎች እና አውቶማቲክ የተኩስ ድምጽ በመዲናዋ የተሰማ ሲሆን ፥ ትምህርት ቤቶችም ተዘግተው በትሪፖሊ የነበረው የትራንስፖርት እንቅስቃሴም ዝቅተኛ እንደነበር ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
ቀውሱ ሊቢያን ከሁለት ዓመታት አንፃራዊ ሰላም በኋላ በምስራቃዊ ሊቢያ በሚደገፈው የባሻጋ መንግስት እና በአብዱልሀሚድ አል ዲቤባህ ስር በሚመራው የትሪፖሊ አስተዳደር መካከል ከባድ ውጥረት ይፈጥራል ተብሏል፡፡
አሁን የተፈጠረው ውጥረት ከወዲሁ የሊቢያን የነዳጅ ዘይት ተቋማት በከፊል እንዲዘጉ ምክንያት ሲሆን፥ ይህም የሊቢያ ዋና የገቢ ምንጭ የሆነው ነዳጅ በግማሽ እንደቀነሰው ተዘግቧል።
በአፍሪካ እጅግ የተትረፈረፈ ሀብት ያላት ሊቢያ በአውሮፓውያኑ በ2011 የሙአመር ጋዳፊ አገዛዝ ከወደቀ በኋላ በተከሰቱት የፖለቲካ ቀውሶች እስካሁን መረጋጋት አለመቻሏን አፍሪካ ኒውስ እና ፍራንስ 24 ዘግበዋል፡፡