Fana: At a Speed of Life!

ራስ ምታትን ለማስወገድ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ራስ ምታት በሚከሰትበት ጊዜ ወደ ሐኪም ቤት ሳይጓዙ ቀለል ያሉ ነገሮችን በማድረግ ህመሙን ማስታገስ ይችላሉ፡፡

ቀዝቃዛ ነገሮችን በራስ ላይ መጠቅለል፦ የራስ ምታት ወይም ከፍተኛ ማይግሬን በሚያጋጥምበት ጊዜ ቀዝቃዛ ነገሮችን በግንባር ላይ በመጠቅለል የህመሙን ስሜት መቀነሰ ይችላሉ፡፡

ቀዝቃዛ ውሃ በፎጣ በመጠቅለል ግንበር ላይ ማሰር ፣ የበረዶ ኩቦችን ራስ ላይ መያዝ እንዲሁም በቀዝቃዛ ውሃ ገላን በመታጠብ ለ15 ደቂቃ ዕረፍት ማድረግ ራስ ምታቱን ማስታገስ ይችላሉ።

ከሳይነስ ጋር የተያያዘ  የራስ ምታት ካለብዎ ሞቅ ያለ ውሃ በግንባር ላይ መያዝ ወይም ለብ ባለ ውሃ በመታጠብ እረፍት ማድረግ ይመከራል።

ጭንቅላት ላይ ያለውን ጫና መቀነሰ፦ ኮፍያ ማድረግ፣ የጭንቅላት ማሰሪያ መጠቀም እና ጥብቅ ያሉ መነፅሮችን ማድረግ የራስ ምታትን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡

ደብዛዛ መብራት መጠቀም፦  በኮምፒውተር እና በስልክ ስክሪኖች ላይ የሚገኙ እና የሚያብረቀርቁ ምስሎች፣ እንዲሁም ከፍተኛ ብርሃን ያላቸው የቤት መብራቶች የራስ ምታትን ያስከትላሉ፡፡

ለእነዚህ ተጋላጭ ከሆኑ ቀን ላይ መስኮቶችን በጥቁር መጋረጃ መሸፈን፣ ከቤት ውጭ የፀሐይ መነፅር መጠቀም የሚያስከትሉትን ጉዳት መቀነስ ይችላሉ፡፡

ማስቲካ አብዝቶ አለማኘክ፦ ማስቲካ አብዝቶ ማኘክ ከመንጋጋ በተጨማሪ ጭንቅላትን ሊጎዳ የሚችል በመሆኑ በሚያኝኩበት ጊዜ ፍጥነትን መቀነስ እና በትንሽ ሀይል ማኘክ ይመከራል፡፡

ማታ ላይ ጥርስዎን የሚያፋጩ ከሆነም የጥርስ ሀኪሞችን ማማከር ይኖርብዎታል፣ይህን በማድረግ በጥዋት የሚከሰተውን የራስ ምታት መቀነስ ይችላሉ፡፡

ውሃ በደንብ መጠጣት፦ ውሃ እና ፈሳሽ ነገሮችን አለመጠጣት የሰውነት ድርቀትን በማምጣት የራስ ምታትን ሊያስከትል ይችላል፡፡

በመሆኑም የራስ ምታትን ለመከላከል ውሃ በብዛት እና ፈሳሽ ነገሮችን መውሰድ ተገቢ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

አነቃቂ የሆኑ ትኩስ ነገሮችን መጠቀም፦  የራስ ምታት ስሜት በሚሰማዎት ጊዜ እንደ ሻይ ፣ ቡና እንዲሁም የካፌይን ንጥረ ነገር ያለባቸውን ትኩስ መጠጦች መጠቀም ህመሙን ሊቀንስልዎት ይችላል፡፡

በተጨማሪም ራስን ማዝናናት፣የራስ ቅልን ማሳጅ ማድረግ፣ የዝንጅብል ሻይ መጠቀም እንዲሁም የራስ ምታት መድሃኒቶችን መውሰድ ራስ ምታትን ለመከላከል እንደሚረዳ የዌብ ሚዲሲን መረጃ ያመላክታል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.