Fana: At a Speed of Life!

የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ መንስዔ እና መከላከያ መንገዶች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሁን አሁን ወጣቶችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ ሳቢያ ለህልፈት የመዳረጋቸው ዜና በተደጋጋሚ ይደመጣል።

ከዚህ ባለፈም ከአጋጣሚው በህይወት ተርፈው የተወሰነ የሰውነት ክፍላቸው አልታዘዝ ብሏቸው በሰው እርዳታ ነገሮችን ሲከውኑም ይታያል።

ይህ አጋጣሚ በምን ሁኔታ ተከሰተ የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ነው።

የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ (ስትሮክ) በደም ቧንቧ መዘጋት የደም አቅርቦት በአግባቡ ወደ አዕምሮ መድረስ ሳይችል ሲቀር የሚከሰት መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በዚህ አጋጣሚ ከሚጠቁ 80 በመቶ ያህሉ ሰዎች “ኢስኬሚክ” በሚባለው ዓይነት የሚጠቁ መሆናቸውንም ነው የሚገልጹት።

እንደ ህክምና ባለሙያዎቹ አጋጣሚው የሚከሰተው በደም ሥር ውስጥ በሚፈጠር የደም መርጋት ሲሆን፥ የረጋው ደም በደም ሥር ውስጥ ተዘዋውሮ አዕምሮ ጋር ሲደርስ የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ (ስትሮክ) ይፈጠራል፡፡

በሥብ ክምችት እና በኮሌስትሮል ምክንያት የደም ሥር ሲጠብና ሲዘጋ አዕምሮ በበቂ ኦክስጅን የበለጸገ ደም ባለማግኘቱ ምክንያትም ይከሰታል፡፡

20 በመቶ ያህሉ በጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ የሚጠቁ ሰዎች ደግሞ በሁለተኛው ወይም ሄሞራጂክ በተባለው የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ ዓይነት እንደሚጠቁም መረጃዎች ያመላክታሉ።

“ሄሞራጂክ” በደም ግፊት ምክንያት የሚያጋጥም ሲሆን አዕምሮ ውስጥ ደም ሲፈስ ወይም በአዕምሮ ውስጥ ያለ የደም ሥር ሲያብጥና የአዕምሮን ክፍል ሲጫን ሕመሙ ይከሰታል፡፡

ይህኛው ዓይነት የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ እጅግ አደገኛና ለሞት የሚያደርስ መሆኑንም ነው የሚነገረው፡፡

እንዴት መከላከል ይቻላል?

የጤና ምርመራ ማድረግን የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የደም ምርመራ ማድረግ፣ በተለይም የቀይ እና የነጭ ደም ሴሎችን መጠን እንዲሁም የደም ግሉኮስ እና የኮሌስትሮል መጠንን ማወቅ።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የሥኳር መጠንን መከታተል፣ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ በምግብ ውስጥ የምንጠቀመውን የጨው እና የቅባት መጠን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡

ሕመሙ ካጋጠመ

ሐኪም በማማከር እንደሁኔታው የደም ወይም የፕላትሌት ማቅጠኛ መውሰድ መጀመር ያስፈልጋል፡፡

ታማሚው መድሃኒቱን መውሰድ ከጀመረ በኋላ በራሱ ፈቃድ እንደፈለገ ማቋረጥ እንደሌለበትና ካደረገው ግን አደጋ እንደሚያስከትል የሜዲካል ኒውስ ቱደይ እና ሄልዝ ላይን መረጃ ያመላክታል።

የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስን በሲቲ ስካን ፣ ካሮቲድ ዱፕሎክስ ስካን፣ ኤም አር አይ እንዲሁም የልብ ምትን ለመመርመር በኤሌክትሮ ካርዲዮግራም በመመርመር መለየት ይቻላል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.