Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት ዳግም ጦርነት ማወጁ ለሰላም ቦታ የማይሰጥ መሆኑን ያረጋግጣል- የጋምቤላ ክልል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት የመንግስትን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው ዳግም ጦርነት ማወጁ ለሰላም ቦታ የማይሰጥ መሆኑን ማረጋገጫ ነው ሲል የጋምቤላ ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ገለጸ።
 
የጋምቤላ ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ላይ ባወጣው መግለጫ፥የሽብር ቡድኑ የከፈተውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የፌዴራል መንግስት የሚያደርገውን ጥረት የሚያደንቅና ከኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ጋር በመሆን የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጅ መሆኑን አረጋግጧል።
 
አሸባሪው የህወሓት ቡድን የቀረበለትን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው ዳግም ወረራ መጀመሩ ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለመበታተን ወደ ኋላ እንደማይል በግልጽና በአደባባይ ያሳየበት እንደሆነም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
 
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
 
በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ላይ ከጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ!
 
አሸባሪው ህወሓት የመንግስትን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው ዳግም ጦርነት ማወጁ ለሰላም ቦታ የማይሰጥ መሆኑን ማረጋገጫ ነው- የጋምቤላ ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
 
የጋምቤላ ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በመግለጫው እንዳለው በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መንግስት የጀመረውን የሰላም አማራጭ በመተው አሸባሪው ህወሃት ሰላም እንደማይፈልግ አረጋግጧል።
 
በቅርቡም በጋምቤላ ከተማ በተላላኪዎቹ በጋ.ነ.ግ እና በሸኔ የሽብር ቡድኖች ሊደርስ የነበረውን የከፋ ጥቃት በፀጥታ ሀይሉ እና በህብረተሰቡ የተቀናጀ ጥረት ማክሸፍ ተችሏል።
 
አሸባሪ ቡድኑ በተለይም የትግራይ ክልል ወጣቶችና አጠቃላይ ህዝቡን ለማያባራ እልቂትና የከፋ ችግር በመዳረግ የራሱን ህልውና ለማስቀጠል እየሰራ ይገኛል።
 
በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰላም ወዳድ በመምሰል የሚያሰራጨው መረጃ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት የሚጠቀምበት ስልቱ እንደሆነም በመግለጫው አመልክቷል።
 
አሁን ላይ የመንግስትን የሰላም አማራጭ ባለመቀበል ጦርነት መክፈቱ የቡድኑን አረመኔያዊነት ያመላክታል።
 
ወገናችን የሆነው የትግራይ ህዝብ የሰላም አማራጭን ባለመቀበል ዳግም ጦርነት የከፈተውን ቡድን በአንድነት ሊያወግዘውና ሊቃወመው ይገባል።
 
አሸባሪው ህውሃት ዳግም በከፈተው ጦርነት ሳንሸበር የአንድነትና የመተሳሰብ እሴታችን ይበልጥ ማጠናከር ይኖርብናል።
 
የዜጎች ደህንነትን ለመጠበቅ ሲል የፌደራል መንግስት የሚወስደዉን ህጋዊ እርምጃዎችን በፅኑ የሚደግፍ መሆኑን የጋምቤላ ህዝቦች ብራዊ ክልላዊ መንግስት ያረጋግጣል።
 
የሽብር ቡድኑ የከፈተውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግስት የሚያደርገውን ጥረት የጋምቤላ ክልል ህዝብና መንግስት የሚያደንቅ ሲሆን ከኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ጋር በመሆን የሚጠበቅበትን ይወጣል።
 
የጋምቤላ ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
 
ነሀሴ 22/2014 ዓ.ም
 
ጋምቤላ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.