” የትግራይ ተወላጆች የአሸባሪው ህወሓት አገር የማፍረስ ተልዕኮን በፅኑ ሊያወግዙ ይገባል” – አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ፣ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ተወላጆች የአሸባሪው ህወሓት አገር የማፍረስ ተልዕኮን በፅኑ ሊያወግዙ እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በአቦከር ወረዳ ከሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ህወሓት አገር ለማፍረስ እያደረገ ያለውን የጥፋት ተልዕኮ በማውገዝ የትግራይ ተወላጆች ከፌደራል መንግሥት ጎን መቆም እንደሚገባቸው አቶ ኦርዲን አሳስበዋል።
የትግራይ ህዝብ እና ህወሓት የተለያዩ ናቸው ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል ።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ዓላማ ለሌለው ጦርነት ህፃናትን አስታጥቆ ማሰለፉን ያነሱት አቶ ኦርዲን፥ በሀረሪ ክልል የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ከክልሉ መንግስት ጎን በመቆም የቡድኑን አካሄድ ማውገዝ ይገባልም ነው ያሉት።
የአቦከር ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሱልጣን ሳኒ ÷ በወረዳው ነዋሪ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች የአሸባሪው ህወሓት የጥፋት ድርጊትን በፅኑ ማውገዝ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ለአካባቢያቸው ለሚከናወኑ የሰላም ተግባራት ቅድሚያ በመስጠት የትግራይ ተወላጆች ከመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ጎን ሊቆሙ እንደሚገባም አቶ ሱልጣን ጥሪ አቅርበዋል ።
በወረዳው ነዋሪ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች በበኩላቸው፥ የአሸባሪው ህወሓት አገር የማፍረስ ተልዕኮን በፅኑ እንደሚያወግዙ በመግለፅ ከመንግሥት ጎን በመቆም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ማረጋገጣቸውን ከአቦከር ወረዳ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡