የጉሮሮ አለርጂ ምልክቶች እና መፍትሄው
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉሮሮ አለርጂ ጉሮሯችን ለአለርጂ ተጋላጭ ሲሆን ምላሽ የሚሰጥበት ምልክት ነው፡፡
የተለያዩ አይነት አለርጂዎች እንዳሉ የህክምና ባለሙያዎች የሚናገሩ ሲሆን÷ ከዚህም ውስጥ የአፍንጫ፣ የቆዳ ፣ የጉሮሮ እና ሌሎችንም አለርጂዎች ይጠቅሳሉ።
ከአንገት በላይ ሃኪም የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ ጥላሁን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋርባደረጉት ቆይታ ስለ ጉሮሮ አለርጂ መንስኤ፣ ምልክቶች እንዲሁም ህክምናውን በተመለከተ ሃሳባቸውን አካፍለዋል፡፡
እንደ ዶክተር ደሳለኝ ገለፃ ÷በዋናነት የጉሮሮ አለርጂ መንስዔዎች ጄኔቲክስ (ተፈጥሯችን)፣ የምንኖርበት አካባቢ፣ የምንወስዳቸው መድሃኒቶች፣ የወቅት መቀያየር (ሙቀት ፣ቅዝቃዜ) ፣ ብናኝ/ፍግ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የጉሮሮ አለርጂ ምልክቶች ደግሞ የጉሮሮ መከርከር፣ ማሳከክ፣ ወፈር ያለ አክታ መኖር፣ ከጉሮሮ ወረድ ብሎ የመተንፈሻ አካል ቱቦ ላይ ሲሆን ደግሞ የድምፅ መጎርነን እና የአየር ማጠር መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
የጉሮሮ አለርጂ መነሻው ከታወቀ ከሚያስነሱብን ነገሮች መቆጠብ ወይም ጥንቃቄ ማድረግ፣ አካባቢን ማፅዳት፣ ከሽታ መራቅ (ጥሩም ሆነ መጥፎ ሽታ) እንደ መከላከያ መንገድ እንደሚያገለግሉ ይጠቅሳሉ።
አለርጂው ከተከሰተ ደግሞ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ በሃኪም የሚታዘዙ መድሃኒቶችን መውሰድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡