የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መማክርት ፎረም በባሕርዳር ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መማክርት ፎረም በባሕርዳር ከተማ ተጀምሯል፡፡
ፎረሙን የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀው ተገልጿል፡፡
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ÷ በኢትዮጵያ የሚገኙ ብዙዎቹ ወንዞች ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚፈሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሐብቶችን ለማልማትና ለመጠቀም በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያን የውሃ ሐብት ተጠቃሚነት መብት ለማስከበርም በርካታ የትብብርና የድርድር ሂደቶች ውስጥ እየታለፈ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የውሃ ሐብትን በፍትሃዊነት ለመጠቀም የሚዲያ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ÷ ከውሃ ሐብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚሰራጩ የተዛቡ መረጃዎችን ለማስተካከል ፎረሙ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው ÷ ዩኒቨርሲቲው በውሃ፣ ውሃ ዲፕሎማሲና ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች መማክርት ፎረም ላይ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የተመሰረቱ ትሥሥሮች መሰል ፎረሞችን እንደሚደግፉም ጠቅሰዋል፡፡
ፎረሙ በውሃና ኢነርጂ ልማት ዘርፍ እንዲሁም በኃይደሮ ዲፕሎማሲ የተሰማሩ ምሁራንን ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የድርድር ሂደት ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎችን እንዲሁም የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችን በማካተት የተመሰረተ ነው ተብሏል፡፡
በተለይም ከውሃ ሐብትና ከኢነርጂ ሐብት ልማት አንጻር፣ ከኅዳሴው ግድብና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ጋር በተያያዘ በዘርፉ ምሁራን፣ በዘርፉ ተዋናዮችና በሚዲያ አካላት መካከል ሊሠሩ በሚገቡ ሥራዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተመላክቷል፡፡
በርካታ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ የዘርፉ ተዋናዮች የሚሳተፉበት መድረክ መሆኑንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡