Fana: At a Speed of Life!

በደም ግፊት የሚመጣ የልብ ድካም እና መፍትሄው

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አንድ ሰው የደም ግፊት ኖሮበት ያ የደም ግፊት የልብ ድካም ሲያመጣ በደም ግፊት ምክንያት የመጣ የልብ ድካም ተብሎ እንደሚጠራ የልብ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ኤሊያስ ጉልማ ይናገራሉ፡፡

ምልክቶቹም እንደ ሌሎቹ የልብ ድካም ህመሞች ከዚህ በፊት ሲሰሯቸው የነበሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማከናወን አለመቻል እንደሆነም ያነሳሉ፡፡

የዚህ በሽታ ተጋላጮች ከዚህ በፊት ሁለት እና ሦስት ደረጃዎችን በሚገባ በበቂ ትንፋሽ ይወጡ ከነበረ አሁን አንድና ሁለት ደረጃን መውጣት ያዳግታቸዋል ብለዋል፡፡

የጡንቻዎች መድከም፣ የልብ ደምን ወደ ፊት ከመርጨት ይልቅ ወደ ኋላ መመለስ ይህም ደም ሳንባ ላይ እንዲከማች በማድረግ ትንፋሽ ማጠር፣ ሳል፣ በሳል ወቅት ደግሞ አብሮ ደም የቀላቀለ አክታ ወይም አረፋ የያዘ አክታ መኖር ሊያስከትል እንደሚችልም አብራርተዋል።

ባስ ሲል ደግሞ በተለይም ወደ ኋላ ሲመለስ ሆድ አካባቢ ውሀ የመያዝ እና እግር የማበጥ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል የዘረዘሩት ባለሙያው እነዚህ በዋናነት ምልክቶቹ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ይህን ለመከላከልም የደም ግፊቱ ወደ መደበኛው እስከሚመለስ ድረስ በሀኪም የታዘዘውን የግፊት መድሃኒት በአግባቡ መውሰድ፣ የሰውነትን ክብደት ማስተካከል፣ በቀን ለ30 ደቂቃ በሣምንት ለአምሰት ቀን በቂ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባ ይመክራሉ።

ከዚህ ባለፈም በደም ውስጥ የሚገኘውን የኮሌስትሮል መጠን በሚገባ መቆጣጠር፣ አብሮ የስኳር ህመም ካለ እሱንም በሚሰጥ መድሃኒትም ሆነ ሌሎች የባለሙያ ምክሮች መቆጣጠር መቻል እንደሚገባ ዶክተር ኤሊያስ ጉልማ ይጠቅሳሉ፡፡

የህክምና ሂደቱም አንድ ሰው አጣዳፊ የልብ ድካም ገጥሞት ወደ ህክምና ማዕከል ሲመጣ የአተነፋፈስ ሁኔታውን አይቶ ሳንባው ስር ያለአግባብ የተከማቸ ውሀ ካለ ያንን ውሀ በሽንት መልክ እንዲወጣ የሚያደርግ መድሃኒት ይሰጣል ብለዋል፡፡

የኦክስጂን እጥረት ካለበትም ኦክስጂን እንዲያገኝ የሚደረግ ሲሆን፥ ልብ ላይም አለአግባብ የተከማቸ ደም ካለ ልብ በአግባቡ ተግባሩን መፈፀም እንዲችል የሚያግዝ ህክምና እንደሚደረግለትም አንስተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም መንስኤ የሆነውን የደም ግፊት ደግሞ ወደ ሚፈለገው ደረጃ ማውረጃ መድሃኒት መውሰድም የህክምናው አካል መሆኑን ጠቁመዋል።

የድንገተኛ ህክምናውን ያጠናቀቀ ታካሚ በቀጣይ የጤናው ሁኔታ እሽከሚሻሻል አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ህመምተኛው ከድንገተኛ ህልፈት ሊታደገው እንደሚችል ነው ያስቀመጡት፡፡

ደም ግፊት እንዳለበት የታወቀ ሰው ወዲያውኑ የግፊት መድሃኒት እንደማይሰጠውና ከሦስት እስከ ስድስት ወር በሽታውን ሊያባብሱ የሚችሉ ነገሮችን እንዲቀንስ አንደሚደረግ ባለሙያው ያነሳሉ፡፡

ከዚህ በኋላ ለውጥ ከሌለው መድሃኒቱን እንዲወስድ እንደሚደረግ የተናገሩት ባለሙያው የታዘዘለትን መድሃኒት ግን በአግባቡ መውሰድ ተገቢ እንደሆነ መክረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.