Fana: At a Speed of Life!

ኅብረት ሥራ ኮሚሽንና ልማት ባንክ የእንስሳት አልሚ ማኅበራትን በጋራ ለማደራጀት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ90 ከተሞች የእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ አልሚ ማኅበራትን በጋራ ማደራጀት የሚያስችል የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽነር ፍሬዓለም ሽባባውና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው ስምምነቱን ፈርመዋል።
የስምምነቱን አተገባበር አስምልክቶ ከክልል ኅብረት ሥራ ማህበራት የተውጣጡና ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች በቢሾፍቱ ምክክር ማድረጋቸውም ነው የተገለጸው።
የኢትዮጵያ ኅብረት ስራ ኮሚሽን ሀገር አቀፍ የእንስሳት ባለሙያዎች መር የህብረት ስራ ማህበራት ልማት መርሐ ግብር ይፋ አድርጓል።
ኮሚሽነር ፍሬዓለም ሽባባው ÷የእንስሳት ሃብት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት መሰረት እንዲሆን የእንስሳት ሃብትና ተዋጽኦ ልማትን ማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት።
በከተሞች በእንስሳት ሳይንስ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በማደራጀት የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የሚሰራ መሆኑን ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሃንስ አያሌው በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በእንስሳትና የተዋጽኦ ልማት ላይ ለውጥ እንዲመጣ ከኢትዮጵያ ኅብረት ስራ ኮሚሽን ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ ሳለ አቅሙን የሚመጥን ለውጥ ያልታየበት ዘርፍ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
የፕሮጀክቱ እውን መሆን በእንስሳት ሳይንስ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ዘመናዊ የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርታማነትን ለማሳደግ ይረዳል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.