Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ 30 ሃገራት የሚያደርገውን በረራ አቋረጠ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ 30 ሃገራት የሚያደርገውን በረራ ማቋረጡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከየትኛውም ሃገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች ለ14 ቀናት በልዩ ማቆያ የመቆየት ግዴታ ተጥሎባቸዋልም ነው ያሉት።

በዚህ ቆይታቸውም ሙሉ በሙሉ ወጪያቸውን ራሳቸው የሚሸፍኑ ይሆናልም ብለዋል።

አያይዘውም በማረሚያ ቤቶች፣ ቫይረሱ ከገባ ለቁጥጥር አስቸጋሪ ሁኔታ የሚፈጠር በመሆኑ ህጻናትን የያዙ፣ የአመክሮ ጊዜያቸው የደረሰና ቀለል ያለ ክስ ያለባቸው እንዲለቀቁ መወሰኑንም አስታውቀዋል።

የእምነት ተቋማትም እንደየአምልኳቸው ሁኔታ ለቫይረሱ ስርጭት ምቹ ሊሆኑ ስለሚችሉ የራሳቸውን ውሳኔ እንዲያሳልፉም ከስምምነት መደረሱን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስታወቁት።
ከዚህ በተጨማሪም የምሽት መዝናኛ ክለቦች አገልግሎት እንዳይሰጡ ተከልክሏል።

ቫይረሱ ከተከሰተ በኋላ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና ማስከተሉንም በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ለአብነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ በቫይረሱ መቀስቀስ ምክንያት ከ190 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ማጣቱን ጠቅሰዋል።

የወጪ ንግድ ዘርፉን በተለይም የአበባ እና የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ተቀባይ ሃገራት ምርቶቹን መቀበል በማቆማቸው ዘርፉ መቀዛቀዙን አንስተዋል።

ከዘንድሮው ሃገር አቀፍ ምርጫ ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያ ምርጫ ቦርድ የራሱን ግምገማ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ ችግሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚታለፍ ከሆነ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ቢካሄድ ጥሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሆኖም አጠቃላይ ውጤቱን ምርጫ ቦርድ በሚያቀርበው ጥናት ላይ በመመስረት ውይይት ተደርጎ ውሳኔ እንደሚተላለፍበት አመላክተዋል።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘም በውጭ ሃገራት ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን መገለል እና ጥቃት አውግዘው፥ ቫይረሱ ቀለም፣ ጾታ እና ሃይማኖት የማይለይ በመሆኑ ማንኛውም ሰው ከዚህ አይነቱ ድርጊት እንዲቆጠብም አሳስበዋል።

ህገ ወጥ ነጋዴዎችን በተመለከተም እንዲህ አይነት ዓለም አቀፍ ፈተና ሲገጥም ሰው ያለውን የሚያካፍልበት እንጅ ከሌላው የሚዘርፍበት ወቅት መሆን አይገባውም ብለዋል።

ህግን ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይም የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስታወቁት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የለይቶ ማቆየና የህክምና ቦታዎች በክልሎችም እየተደራጁ መሆኑንም አውስተዋል።

ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየተገኘ ካለው ድጋፍ ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያም፥ ከጃክ ማ እና ቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን እንዲሁም ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን በመጥቀስ፥ በመጭው እሁድ ጠዋት የጃክ ማ ፋውንዴሽን ካደረገው የመመርመሪያ መሳሪያ እና የፊት ጭምብል ድጋፍ የተወሰነ ቁጥር እንደሚገባም አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በዛሬው መግለጫቸው በስራ ላይም ሆነ በትምህርት ላይ ያሉ የህክምና ባለሙያዎችን አመስግነው የቫይረሱ ስርጭት ተጨማሪ ጥረት ስለሚጠይቅ ራሳቸውን ለሀገራዊ ግዳጅ እንዲያዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል።

የግል ሆስፒታሎችም አቅማቸው በፈቀደ መጠን እንዲዘጋጁም ነው ያሳሰቡት።

ሁሉም ተባብሮ ዜጎች ለህልፈት እንዳይዳረጉ መስራት እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።

 

በአላዛር ታደለ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.