Fana: At a Speed of Life!

15ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በነገው ዕለት ይከበራል

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 15ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በነገው ዕለት በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

በዓሉ “ሰንደቅ ዓላማችን የብዝሃነታችን መገለጫ የሉዓላዊነታችን ምሰሶ ነው!” በሚል መሪ ቃል ነው የሚከበረው፡፡

በዓሉ ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታን በዋጀ መልኩ ለ15ኛ ጊዜ በፌደራል፣ በክልሎችና በሁለቱም የከተማ አስተዳደር ከተሞች ከሰንደቅ ዓላማ መርሆዎች ጋር ተገናዝቦና ሀገራዊ ሪፎርሙን በሚያስቀጥሉ ውይይቶች ታጅቦ በየተቋማቱ እንደሚከበር ተጠቁሟል፡፡

የውስጥ ቅጥረኛች ተላላኪዎቻቸውን ይዘው በቅርብም ከሩቅም ያሉ የውጭ ጠላቶቻችን አቅደውና ተናበው ብሔራዊ አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን አደጋ ላይ ለመጣል እየሰሩ ባሉበት በዚህ ወቅት የሰንደቅ ዓላማ ቀን መከበሩ ለሕብረብሄራዊ አንድነታችን መጠናከር፣ ለሉዓላዊነታችን መከበርና ይበልጥ ብሔራዊ መነቃቃትን ለመፍጠር ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑንም ምክር ቤቱ አውስቷል፡፡

በዓሉ ለሀገር ክብርና ጥቅም ሁላችንም እንደዜጋ የበኩላችንን ለመወጣት በሰንደቅ ዓላማ ፊት ዳግም ቃላችንን የምናድስበት ዕለት ይሆናል መባሉንም ከምርክ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት በመላው ሀገሪቱ የሚከበር መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ስለሆነም በፌደራል የመንግስት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች፣ በመከላከያ ሰራዊት ካምፖች እንዲሁም በኤምባሲዎችና የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ከረፋዱ 4፡30 ላይ ሰንደቅ ዓለማ በመስቀልና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም ስነ-ስርዓት እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር ምክር ቤቱ አስገንዝቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.