በዓለም ላይ በከሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ300 ሺህ ሲያልፍ፤ 93 ሺህ ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ300 ሺህ በላይ ማለፉን መረጃዎች እየጠቆሙ ነው።
በአሁኑ ወቅት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከ13 ሺህ የበለጠ ሲሆን፥ ከ93 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ከበሽታው አገግመው ወደ ቤታቸው መመለሳቸው ነው የተገለፀው።
ስፔን በዓለማችን በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ተጎድተዋል ከሚባሉት የዓለም ሀገራት ውስጥ አንዷ ስትሆን እስካሁንም 28 ሺህ 572 ታማሚዎች ሲኖሩ፤ ከ1 ሺህ 700 በላይ ሰዎችን ደግሞ አጥታለች።
በስፔን በዛሬው እለት ብቻ በአንድ ቀን 394 ሰዎች በኮሮናቫይረስ አማካኝነት ያጣች ሲሆን፥ ሀገሪቱ በሽታው ከዚህም በላይ ሊስፋፋ ይችላል በሚል የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ከእነዚህም ውስጥ በማድሪድ ከተማ የሚገኘውን የሀገሪቱን ትልቁ የኮንፈረንስ ማእከል ወደ ተኝቶ መታከሚያነት በመቀየር አልጋ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን አዘጋጅታለች።
5 ሺህ 500 አልጋዎችን የያዘው ጊዜያዊ ሆስፒታሉ ከአውሮፓ ትልቁ ነው ተብሏል፤ 300 ታማሚዎችም በዚህ ሁለት ቀናት ወደ አዲሱ ሆስፒታል እንዲገቡ ይደረጋልም ነው የተባለው።
አውስትራሊያ በበኩሏ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የምሽት ጭፈራ ቤቶች እና መጠጥ ቤቶችን፣ የቁማር ቤቶችን፣ ሲኒማ ቤቶችን እና የአምልኮ ስፍራዎችን ልትዘጋ ሲሆን፥ ዜጎቿ ከቤት እንዳይወጡ የሚል ውሳኔ ማሳለፏም ተሰምቷል።
ብሪታኒያም አሁን ላይ ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ እየታዩ ያሉ አሃዞች አስጊ መሆኑን በመግለፅ፤ ዜጎቿ የበለጠ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስባለች።
ምንጭ፦ ቢቢሲ