የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርን አኅጉር አቀፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ -ግብር አኅጉር አቀፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ይህን ዓላማ ይዞ ወደ ሶማሊያ ያቀናው የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ዲፕሎማሲ የወጣቶች ልዑክም ሞቃዲሾ ገብቷል፡፡
ልዑኩ በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አብዱልፈታህ አብዱላሂ እና በሶማሊያ የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዴኤታ አደም ኢብራሂም ሂርሴ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡
በመርሐ-ግብሩ ላይ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደር አብዱልፈታህ አብዱላሂ ኢትዮጵያውያንን እና ሶማሊያውያንን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ይበልጥ ለማስተሳሰር የልዑካን ቡድኑ መምጣት ይበልጥ አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በቆይታቸውም አረንጓዴ ዐሻራቸውን ከማሳረፍ ባለፈ ወንድማማችነትን የሚያጠናከር የተሞክሮ ልውውጥ እና የፓናል ውይይት ይካሄዳል ብለዋል።
በሶማሊያ የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዴኤታዉ አደም ኢብራሂም ሂርሴ በበኩላቸው፥ ሀገራቸው በትናንትናው ዕለት ሰፊ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር መጀመሯን ጠቅሰዉ የኢትዮጵያው ልዑክ ወደሞቃዲሾ መምጣቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀልበስ ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።
ሁለቱ ህዝቦች አንድ ናቸዉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታወ፥ ልዑካኑ በመምጣታቸው ደስ መሰኘታቸውንና፣ እንዲህ ያሉ ተልዕኮዎች አፍሪካ በቀጣይ ለምታደርጋቸዉ የአየር ንብረት ለዉጥ ተጨባጭ ለዉጥ መማጣት እንደሚችሉ ዕምነታቸዉን ተናግረዋል ።
በፀጋዬ ወንድወሰን