Fana: At a Speed of Life!

ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት ያላትን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንሰራለን- የጅቡቲ ሉዓላዊ ፈንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ጥብቅ የባህል፣ የቋንቋና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር በንግድና ኢንቨስትመንት ለመድገም እንደሚሰራ የጅቡቲ ሉዓላዊ ፈንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስሊም ፌሪያኒ ተናገሩ።

ጅቡቲ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ቀጣናዊ ውህደትን የሚያፋጥኑ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ቀርጻ እየተገበረች ትገኛለች ።

ከመርሐ ግብሩ መካከልም በጅቡቲ ፕሬዚዳንት ከሁለት ዓመት በፊት ይፋ የተደረገው የጅቡቲ ሉዓላዊ ፈንድ አንዱ ሲሆን÷ ከጅቡቲ ባለፈ በሌሎች የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በተለያዩ መስኮች ኢንቨስትመንት ለማስፋት ያለመ ነው።

ፈንዱ በዋናነት ጅቡቲ ከመርከብ ጭነትና ወደብ አገልግሎት ባለፈ በቴሌኮም፣ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ በኃይል፣ በመሰረተ ልማት፣ በሎጂስቲክስ፣ ግብርናና ዓሳ ምርቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግን ያካተተ ነው።

ኢንቨስትመንቱ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የሚጠይቅ ሲሆን በሚቀጥሉት 10 ዓመታት የሚተገበር መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የጅቡቲ ሉዓላዊ ፈንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስሊም ፌሪያኒ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት የበለጠ ተቀራርባ ለመስራት ትሻለች።

”በጉብኝቴ ኢትዮጵያ ውስጥ በሪል ስቴት፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በቴሌኮምና በሌሎች መስኮችም የበለጠ መስራት የሚቻልባቸው እድሎች መኖሩን አይቻለሁ” ብለዋል።

ኢትዮጵያና ጅቡቲ ስትራቴጂያዊ አጋር መሆናቸውን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ÷ይህም ለሌሎች አፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል ።

በተለይም አፍሪካውያን መጻኢ እድላቸውን ብሩህ ለማድረግ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው÷ የኢትዮጵያና የጅቡቲ ግንኙነት አንድ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው በኢንቨስትመንትና ንግድ ዘርፍ ትልቅ አቅም ያላት አገር ናት ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት ያላትን ግንኙነት የበለጠ ማሳደግ እንደምትፈልግ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የጁቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት 60 በመቶ የሚሆነው የጁቡቲ ሉዓላዊ ፈንድ ኢንቨስትመንት በተለያዩ አፍሪካ አገራት በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚተገበር ነው ማለታቸውን አስታውሰዋል።

በፈንዱ ኢንቨስት ከሚደረገው ውስጥ 20 በመቶ በኢትዮጵያ ላይ ለማድረግ መታቀዱን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው÷ ይህም የሁለቱ አገራት አጋርነት ምን ያህል ጠንካራ መሆኑን አመላካች ነው ሲሉ ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.