በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለማቋቋም የጋምቤላ ክልል መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል-አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ተናገሩ።
ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት÷ የጋምቤላ ክልል የትግራይን ህዝብ ጨምሮ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለማቋቋም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የጋምቤላ ክልል መንግስትና ህዝብ የተደረሰው የሰላም ስምምነት በአግባቡ ተፈፃሚ እንዲሆን በሙሉ ልብ እንደሚደግፍ ነው ያስታወቁት፡፡
አሁን የተደረገው ስምምነት የእናቶችን እምባ የሚያብስ፣ የሕፃናትን ሰቆቃ የሚያቆም እንዲሁም በወንድማማች ህዝቦች መካከል የተከሰተውን ደም መፋሰስ ለማቆም መሰረት የሚጥል መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በጦርነቱ ምክንያት የደረሰውን ኪሳራ ለማካካስ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
የሕይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ የጸጥታ ሃይሎች እውቅና መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው÷ የክልሉ ህዝብ ለሀገር መከላከያ ሰራዊቱ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠይቀዋል።
አቶ ኡሞድ የሰላም ስምምነቱ በዚህ መልኩ እንዲጠናቀቅ ለደከሙና የህይወት ዋጋ ለከፈሉ ሁሉ ምስጋና ማቅረባቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡