Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል የሕክምና መድሃኒትና ቁሳቁስ የማቅረብ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል – ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል አስፈላጊ የሕክምና መድሃኒቶች እና ቁሳቁስ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

መንግስት ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዚሁ መሰረት በመጀመሪያው ዙር÷ ሚኒስቴሩ ከብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመሆን 6 ሚሊየን 433 ሺህ 408 ብር ከ47 ሣንቲም ግምት ያላቸው ሕይወት አድን መድኃኒቶችንና የህክምና ግብዓቶችን ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የክምችት መጋዘን ለሽረ ቅርንጫፍ ማድረሱ ተገልጿል፡፡

በሁለተኛው ዙርም÷ ከ 1 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የጤና አገልግሎት ግብዓቶችን በመላክ ለሽረ ሆስፒታልና ዘጠኝ ጤና ጣቢያዎች በማድረስ ማህበረሰቡ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡

እንዲሁም ለሦስተኛ ጊዜ÷ ጤና ሚኒስቴር ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመሆን ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የህክምና መድኃኒቶች እና ቁሳቁስ በመጓጓዝ ላይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

እንዲሁም በዚህ ሳምንት በዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በኩል 33 ነጥብ 9 ሜትሪክ ቶን መሰረታዊ የህክምና እቃዎች፣ የአስቸኳይ ጊዜ መድሃኒቶች እና የቀዶ ጥገና መሳሪዎችን የጫኑ ሁለት ከባድ ተሽከርካሪዎች መቀሌ መድረሳቸውም ተመጠቅሷል፡፡

ሌሎች የአለም አቀፍ ድርጅቶችና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትም ተጨማሪ ሰብዓዊ ድጋፍ ለመላክ ዝግጁ ማድረጋቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

የጤና ተቋማትን መልሶ ለማደራጀት እና አገልግሎት ለማስጀመር ከተለያዩ የሥራ ክፍሎች የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች እና ሠራተኞች ወደ ስፍራው ማቅናታቸው ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.