Fana: At a Speed of Life!

አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በቀጣዩ አመት ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍሎች ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ይሆናል ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 8 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በ2016 ዓ.ም ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍሎች ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

31ኛው አገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ተጀምሯል።

የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በዩኒቨርሲቲዎች ያለውን የትምህርት ጥራት ችግር ለመቅረፍና በቀጣዮቹ 5 ዓመታት የትምህርት ጥራትና ተገቢነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የለውጥ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንዲሆኑና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና እንዲወስዱ ማስቻል እየተከናወኑ ካሉ ስራዎች መካከል እንደሚገኙበት አመላክተዋል።
”በሁለት ወር ጊዜ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ሆኖ ይደራጃል” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት እንዲሁም በአራት ዓመት ውስጥ ሁሉም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ እቅድ ተይዟል ብለዋል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ትምህርታቸውን ላጠናቀቁ ተማሪዎች በቴክኖሎጂ የታገዘ የመውጫ ፈተና መስጠት ከተያዘው ዓመት ጀምሮ መስጠት እንደሚጀመርም ጠቁመዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል አዲስ ስርዓተ ትምህርት መቀረጹን አንስተዋል።

ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በሙከራ ደረጃ የተጀመረው አዲሱ ስርዓት ትምህርት ዘንድሮ ወደ ሙሉ ትግበራ እንደተገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.