Fana: At a Speed of Life!

የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ቀጣይ ልማት ለማሸጋገር ፖሊሲዎችን በድጋሚ ማየትና መከለስ ያስፈልጋል – ለሊሴ ነሜ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ቀጣይ ልማት ለማሸጋገር ፖሊሲዎችን በድጋሚ ማየት እና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን መከለስ አስፈላጊ መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የልዩ ኢኮኖሚክ ዞን ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
 
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ÷ባለፉት ዓመታት መንግስት ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ስርዓት መዘርጋት መቻሉን አንስተዋል ።
 
በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርክ ተሞክሮ ውስን ዕድሜ ያለው መሆኑን ጠቁመው ÷ ዘርፉ የሀገሪቷን የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት ላይ ትልቅ ድርሻ እየተጫወተ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡
 
በተለይም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ማዕቀፍ መጥበቡ እና በውስን ሴክተሮች ላይ ብቻ ማተኮሩ የሚፈለገውን ውጤት እንዳያመጣ አድርጎታል ነው ያሉት።
 
ስለሆነም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ቀጣይ ልማት ለማሸጋገር ፖሊሲዎችን በድጋሚ ማየት እና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን መከለስ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
 
ረቂቅ ህጉ በተግባር ያሉ ክፍተቶችን ከመሙላት ባለፈ በተለያዩ ዘርፎች የኢንቨስትመንት ተሳትፎን ለማሳደግ እና ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ በሆነችባቸው ዘርፎች ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ የሚያደርግ ነውም ብለዋል ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.