Fana: At a Speed of Life!

በ180 ሚሊየን ዶላር የሚተገበርና ስደተኞችን እንዲሁም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት 5 ዓመታት በ180 ሚሊየን ዶላር የሚተገበርና ስደተኞችን ብሎም የሚጠለሉበትን አካባቢ ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁለተኛውዙር የስደተኞች ተጽዕኖ ምላሽ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

ፕሮጀክቱ የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ የልማት አጋሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዳማ ከተማ ነው ይፋ የሆነው፡፡

የፕሮጀክቱ ዓላማ በተለያዩ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች በሚኖሩበት አካባቢ ሊከሰት የሚችልን ማህበራዊና አካባቢያዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ የሚረዳ ነው፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን እንደተናገሩት፥ በመጀመሪያ ዙር የፕሮጀክቱ ትግበራ ስደተኞችን ያስጠለሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን የልማት ችግሮች ያቃለሉ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

በአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በሶማሌና በትግራይ ክልሎች ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ውጤት እንደተገኘባቸው ጠቁመዋል።

ለአብነትም 225 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 98 የጤና ኬላዎች፣ 48 የእንስሳት ጤና ኬላዎች፣ 520 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ፣ 220 የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ በፕሮጀክቱ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል እንደሚገኙበት ኢዜአ ዘግቧል።

በተጨማሪም አራት የግብርና ግብዓት ማከማቻ መጋዘንና አምስት አነስተኛ የገበያ ማዕከላት መገንባታቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አንስተው በመጀመሪያው ዙር የፕሮጀክቱ ትግበራ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ዛሬ ይፋ የተደረገው ሁለተኛው ዙር ፕሮጀክት 180 ሚሊየን ዶላር የተመደበለት ሲሆን ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እንደሚተገበርና የገንዘብ ድጋፉ ከዓለም ባንክ የተገኘ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ ስደተኞችን የሚያስጠልሉ ማህበረሰቦችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ በቀጥታ ስደተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ከመጀመሪያው ዙር የተለየ እንደሚያደርገው ተመልክቷል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.