Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ ዕገዳ ለጣለችባቸው የቻይና ገቢ ምርቶች ፍቃድ ልትሠጥ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ ስትል ዕገዳ ለጣለችባቸው የቻይና ምርቶች ዝርዝር ፍቃድ ልትሠጥ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የገቢ ንግድ ዕግዱ የሚነሳው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከቻይናው አቻቸው ሺ ጂንፒንግ ጋር በቅርበት ለመሥራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ተከትሎ መሆኑን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡

አወንታዊ ውሳኔው የጦፈ የንግድ እና የቴክኖሎጂ ውድድር ውስጥ በሚገኙት ሁለቱ ኃያላን ሀገራት መካከል ያለውን ባላንጣነት የሚያረግብና ትብብራቸውን የሚያድስ ነው ተብሎለታል።

ቀደም ሲል አሜሪካ ለቻይና የምታቀርበው ሚስጢራዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ መዋላቸውን ለማረጋገጥ ኩባንያዎችሽን ልፈትሽ የሚል ጥያቄ አቅርባ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በወቅቱ ቤጂንግ ለጥያቄው ይሁንታ ባለመስጠቷ ዋሺንግተን በአጸፋው ከጠረጠረቻቸው የቻይና ኩባንያዎች ምርቶች እንዳይገቡ “ያልተረጋገጡ” የሚል ዝርዝር አዘጋጅታ አግዳ ቆይታለች፡፡

አሁን ላይ ቻይና ኩባንያዎቿ እንዲፈተሹ ፍቃድ በመስጠቷ ዕግዱ እንደሚነሳ የሀገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ተናግረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የአሜሪካ ንግድ ሚኒስቴር አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡

በቤጂንግ እንዲህ ያሉ ፍተሻዎች ይካሄዱ ዘንድ የሀገሪቷን ንግድ ሚኒስቴር ይሁንታ ማግኘት አለባቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.