Fana: At a Speed of Life!

ከገና ጋር የተያያዙ ሐይማኖታዊ ሥርዓቶች በላሊበላ ከዛሬ ጀምሮ በልዩ ሁኔታ ይቀርባሉ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ከገና በዓል ጋር የተያያዙ ሐይማኖታዊ ሥርዓቶች ከዛሬ ምሽት ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ 29 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በሦስት ቤተ ክርስቲያኖች በልዩ ሁኔታ ይከናወናሉ፡፡

በቅዱስ ላሊበላ ደብር የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ እና አስጎብኚ ቀሲስ ፈንታ ታደሰ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ከገና በዓል ጋር በተያያዘ ከዛሬ ምሽት ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ 29 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በቤተ መድኃኔዓለም፣ በቤተ አማኑኤል እና በቤተ ማርያም በልዩ ሁኔታ ይከበራል፡፡

ሁሉም ቤተ ክርስቲያኖች ሥጋ ወደሙ ለማቀበል ሥርዓተ ቅዳሴ እንደሚፈጸምባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

“በገና በዓል በሚቀርቡት ሐይማኖታዊ ሥርዓቶች ሁሉ ተመስጋኙም አምልኮቱም እግዚአብሔር ነው” ያሉት ቀሲስ ፈንታ፥ ገና (ልደት) በላሊበላ ልዩ የሚያደርገው የኢየሱስ ክርስቶስ እና የቅዱስ ላሊበላ ልደት አንድ ቀን መሆኑ ነው ይላሉ፤ የተወለዱበትን ዓመተ ምህረት መለያየት ልብ ይሏል ነው ያሉት፡፡

በሐይማኖቱ ስነ ስርዓት መሠረት በዚሁ የልደት በዓል አከባበር ላይ ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ገብረ ማርያም፣ ቅዱስ ላሊበላ እና ቅዱስ ነአኩቶሎአብ ይመሰገናሉ ብለዋል፡፡

የቅዱስ ላሊበላ የመጀመሪያ ሥራ በሆነችው በቤተ ማርያም ዙሪያ ታኅሣሥ 28 ለ29 አጥቢያ ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ መድኃኔዓለም (የዓለም መድኃኒት፣ የዓለም ሁሉ ቤዛ ዛሬ ተወለደ) እየተባለ ምስጋና ይቀርባል፤ ይህም በላሊበላ ከተማ የሚከበረውን የገና በዓል ልዩ እንደሚያደርገው ነው ያስረዱት፡፡

ልክ ከሰማይ መላዕክት እንደሚመጡ በቤተ ማርያም ዙሪያ ባለው ማሜ ጋራ ካኅናቱ ካባና ሸማ በመልበስ እያሸበሸቡ እየሰገዱ ወደታችና ወደላይ ሲቃኑ በመላዕክት ምሳሌ ሥርዓቱን ያቀርባሉ ሲሉም አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም ከታች ያሉት ካኅናት ሰባሠገልን ተመስለው አምሐ ይዘው ኮከብ እየመራቸው ወደ ቤተልሔሙ እንደሔዱ በመምሰል ሥነ ስርዓት ይከናወናል ብለዋሎ፡፡

እንደ ቀሲስ ፈንታ ታደሰ ገለጻ÷ ወደ ላሊበላ ከተማ እየገቡ ያሉ እንግዶች በከተማዋ ነዋሪዎች እና ቀድመው በገቡ እንግዶች ጭምር እግር ማጠብን ጨምሮ በሀገርኛ የእንግዳ አቀባበል ዘይቤ እየተስተናገዱ ነው፤ በእግር አጠባው ላይ የውጭ ዜጎችም እየተሳተፉ ነው፡፡

የጎብኚዎችን ቆይታ በመረጃ የዳበረ እና የተሳለጠ እንዲሆን ከ191 በላይ አባላት ያሉት የቅዱስ ላሊበላ አስጎብኚ ማኅበር ዝግጁ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.