Fana: At a Speed of Life!

ለአሸባሪው ሸኔ ሎጂስቲክ እና መረጃ በማቀበል የተጠረጠሩ 4 ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሽብር ቡድኑ ሸኔ በሎጂስቲክ አቅርቦትና በመረጃ ልውውጥ የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ፍርድ ቤት ከቀረቡት ተጠርጣሪዎች መካከል በምዕራብ ሸዋ ዞን ግንደበረት ወረዳ ነጋዴ የሆኑት ግለሰብ እና የአፋን ኦሮሞ ሙዚቃ ባለሙያ ይገኙበታል።

ተጠርጣሪዎቹ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።

ተጠርጣሪዎቹም 1ኛ የአፋን ኦሮሞ ሙዚቃ ባለሙያ የሆነው ቀነኒሳ አልጃማ ፣ 2ኛ በግል የኤጀንሲ ሥራ የሚሰራው ብርሃኔ ገዛኔ ፣ 3ኛ የምዕራብ ሸዋ ዞን ግንደበረት ወረዳ ነጋዴ የሆኑት አቶ ወንድሙ ባሀ እና በግል ሥራ የሚተዳደረው ገለሱ ኢሊባ ናቸው።

ተጠርጣሪዎቹ ጥር 4 ቀን 2015 በኦሮሚያ ፖሊስ በቡራዩ ከተማ ኬላ ፣ አሸዋ ሜዳና በሌሎች ቦታዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መተላለፋቸው ተገልጿል።

ተጠርጣሪዎችን ከኦሮሚያ ፖሊስ ተረክቦ ምርመራ እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ÷ ተጠርጣሪዎቹ ከኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት በማድረግ መረጃ በመለዋወጥና ሎጂስቲክ በማቅረብ መጠርጠራቸውን ለችሎት አስረድቷል።

ተጠርጣሪዎቹን አሻራ እና ፎቶ ማስነሳቱን የገለጸው መርማሪ ፖሊስ ÷ የባንክ የገንዘብ ዝውውር ካለ ለማጣራት ማስረጃ መጠየቁን ለችሎቱ አብራርቷል።

ከወንጀሉ ውስብስብነት አንጻር የጀመረውን ምርመራ በማስረጃ አጠናክሮ ለማቅረብ የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የአፋን ኦሮሞ ሙዚቃ ባለሙያ ነው የተባለው አንደኛ ተጠርጣሪ ቀነኒሳ አልጀማ ÷ ለሸኔ ግጥምና ዜማ እንድሠራ ልጅ ያሬድ እና ኪያ የሚባሉ ግለሰቦች ጠይቀውኛል ሲል ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

በቁጥጥር ሥር በዋልኩበት ወቅት ከአሸባሪው ሸኔ ከጫካ መልዕክት ይዞልኝ የመጣውን ሰው ለፖሊስ ጠቁሜ ነበር ሲልም ነው ያብራራው፡፡

ቤተሰቦቹ ከምዕራብ ሸዋ በሸኔ ተፈናቅለው እንደመጡ የገለጸው ተጠርጣሪው ቀነኒሳ ÷ የሙዚቃ ሥራ እየሰራ አቅመ-ደካማ ቤተሰቦቹን እንደሚያስተዳድራቸው በመግለጽ ከተጠቀሰው ወንጀል ጋር የሚያገናኘኝ ነገር የለም ሲል ተከራክሯል።

በቀድሞው ሥርዓት በእስር አሳልፎ በ2008 ዓ.ም መፈታቱንም በመግለጽ የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅ ለት ጠይቋል።

በግንደበረት ወረዳ ነጋዴ ናቸው የተባሉት አቶ ወንድሙ ባሀ ÷ በጠበቃ ተወክለው ከወንጀሉ ጋር የሚያገናኛቸው ጉዳይ እንደሌለ ጠቅሰው፤ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።

በተጨማሪም ኦነግ ሸኔን ሸሽተው ከግንደበረት ሐብትና ንብረታቸውን ጥለው መምጣታቸውን አብራርተዋል።

ሌሎችም ተጠርጣሪዎች በተመሳሳይ ከወንጀሉ ጋር የሚያገናኛቸው ጉዳይ እንደሌለ በመግለጽ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ÷ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ምሥክር ሊያባብሉና ምርመራውን ሊያደናቅፉ ይችላሉ ሲል ሥጋቱን ገልጾ የዋስትና ጥያቄያቸውን በመቃወም ተከራክሯል።

ክርክሩን ያዳመጠው የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ እና የፖሊስ የተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ላይ ተወያይቶ ለመወሰን ለከሠዓት በኋላ የቀጠረ ቢሆንም ፣ ከሠዓት በኋላ ላይ ግን የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንዲቀርብለት በማዘዝ መዝገቡን ተመልክቶ ትዕዛዝ ለመስጠት ለነገ በይደር ቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.