Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ድጋፉን እንደሚያጠናክር ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን የሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፀ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ሚርጃና ስፖልጃሪክ ኤገር ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም አቶ ደመቀ መንግሥት የሰላም ስምምነቱን በቁርጠኝነት እየተገበረ መሆኑን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅትም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶች በተጠናከረ መልኩ አገልግሎት እንዲጀምሩ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነትንም የማስፋፋት እና የማጠናከር ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት አቶ ደመቀ፥ በግጭቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባት እና የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ሁሉን አቀፍ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ አጋር አካላት እስካሁን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አቶ ደመቀ መጠየቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት እና በድርቅ ምክንያት ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን ተደራሽ ለማድረግ መንግሥት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ሚርጃና ስፖልጃሪክ ኤገር በበኩላቸው÷ ኮሚቴው ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ሁኔታ ተስፋ ሰጭ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚሹ ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ በማስፋት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.