Fana: At a Speed of Life!

ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ የፌዴራል ተቋማት ግዢ በኤሌክትሮኒክስ መፈፀም ይጀምራሉ- የግዢና ንብረት ባለስልጣን

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ ሁሉም የፌዴራል ተቋማት ግዢን በኤሌክትሮኒክስ መንገድ መፈፀም እንደሚጀምሩ የግዢና ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በያዝነው አመትም 74 የፌዴራል ተቋማት በኤሌክትሮኒክስ ግዢ መፈፀም መጀመራቸው ተገልጿል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ የሀገሪቱን 70 በመቶ በላይ የሚሆነው በጀት የሚውልበት በመሆኑ ግዢን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ማከናወን ከሌብነት የፀዳ ግዢን ለመፈፀም አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ከጨረታ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በምሳሌነት ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ መሰል ችግሮችን መቅረፍ የሚቻለው አሰራርን በማዘመን መሆኑ ታምኖበት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

ባለፈው ዓመት ዘጠኝ ተቋማት በኤሌክትሮኒክስ ግዢ መፈፀም የጀመሩ ሲሆን፤ ስድስቱ ደግሞ በኤሌክትሮኒክስ መንገድ 22 ጨረታዎችን ማውጣት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ የማኑዋል ግዢ ከስራ ውጪ በማድረግ ግዢን ከሌብነት የፀዳ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ስልጠና መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዳግም አላምረው በበኩላቸው ሙስና ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ ስልጠናዎች በተለያዩ ግዜያቶች ኮሚሽኑ በመሰጠት ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

በብርሃኑ በጋሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.